
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓድዋ ድል መታሰቢያ የዓድዋን ታሪክ ለማወቅ ከማገዙ በዘለለ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሕዝብ ኅብረት አስፈላጊነትን እንደሚያስተምር የእስልምና ኃይማኖት መምህራን እና አባቶች ተናገሩ።
ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሰባሰቡ የእስልምና ኃይማኖት መምህራን እና የእምነቱ አባቶች የዓድዋ ድል መታሰቢያን ዛሬ ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ በኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ ሀብት ስለኾነው ዓድዋ ድል ያላቸውን መረጃ ሊያጎለብቱላቸው የሚችሉ እውነታዎችን ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ አብዱላዚዝ አብዱልዋሊ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያንን ማንነት የሚገልጽ ጥልቅ የሀገር ሀብት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
መታሰቢያው ኢትዮጵያዉያን በኅብረት የሀገሪቱን ሕልውና ለማስጠበቅ የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ መኾኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ እርስ በእርስ ያለንን አንድነት ማጠናከር እንዳለብን ትምህርት ይሰጣልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪ እና የኃይማኖት መምህር ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ መታሰቢያው የቀደሙ አባቶች የሀገሪቱን የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ የከፈሉትን ዋጋ ይዘክራል ብለዋል። ዓድዋ በአንድነት ከቆምን እና ተባብረን ከሠራን ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻል ትምህርት መውሰድ የሚያስችል ፕሮጀክት መኾኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ብዙ ሊነገሩ እና መታሰቢያ ሊቆምላቸው የሚገቡ የታላላቅ ታሪኮች ባለቤት ናት ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ እስልም እና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ኡስታዝ መሐመድ አባተ ናቸው።
ኢዜአ እንደዘገበው መታሰቢያው ዓድዋ ሲነሳ ሊታወቅ የሚገባውን መረጃ ያገኙበት መኾኑን እና የሀገሪቱን ታሪካዊ ሀብቶች የሚያሳዩ ሌሎች መታሰቢያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሊሰፉ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!