
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች የሚቋቋሙበት ረቂቅ አዋጅ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 18ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።በመደበኛ ስብሰባውም የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች የሚቋቋሙበትን በተመለከተ በወጣው ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል።
የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ለምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም አዋጁ ለልማት ተነሺዎች ተገቢ የኾነ የካሳ ክፍያ ለማከናወን እንዲሁም የልማት መጓተት ችግርን ለመፍታት መኾኑን አስረድተዋል።
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን አሰራር የሚያሳልጥ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
የመሠረተ ልማት ሥራዎች ሲከናወኑ የንብረት መገመት፣ የመክፈል እና የማስነሳት ሥራ ለክልሎች እና ለከተማ አሥተዳደሮች የሚሰጥ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
በአሠራር ሂደቱ የባለቤትነት ስሜት ለመፍጠር እና ቀልጣፋ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት መኾኑም ተገልጿል።ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ለከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች እና ለሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች መምራቱን ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!