
ደብረ ማርቆስ: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕል እና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለሀገር ሰላም አዎንታዊ ሚና አላቸው። ኢትዮጵያውያን ባሕላዊ የግጭት አፈታት እና የሀገር ሽማግሌዎችን ምክር በመቀበል ለችግሮቻቸው መፍቻ መንገድ አድርገው ሲጠቀሙ ኖረዋል።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህርት ድርቧ ደበበ (ዶ.ር) አሁን አሁን ለነዚህ ባሕላዊ የግጭት አፈታት እሴቶች የሚሰጠው ትኩረት እየቀነሰ ከመምጣቱ ባሻገር በዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶችን ማካተት ላይ ክፍተቶች ይታያሉ ብለዋል።
የሀገር በቀል ዕውቀትን ተጠቅሞ ግጭቶችን ለመቀነስ እና የሀገር ሰላምን ለማስጠበቅ የሚደረገው ጥረትም አነስተኛ ነው ብለዋል።ይህ ደግሞ ሀገር አሁን ለገባችበት ቀውስ እንደ ምክንያት ኾኖ ይነሳል ነው ያሉት፡፡
ባሕላዊ የግጭት አፈታት እሴቶች ለፍትሕ ሥርዓት መጎልበት ያላቸው ሚና ቀላል አይደለም ያሉት ዶክተር ድርቧ ማኅበረሰቡ ለዘመናት ሲገለገልባቸው የቆዩ ሃብቶቹ ናቸው ብለዋል፡፡ እነዚህን እሴቶች ጠብቆ ለማቆየት እና ሀገር ለገባችበት የሰላም ዕጦት መፍትሔ ይኾን ዘንድ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ለዘመናዊው የፍትሕ ሥርዓት መጎልበት ፋይዳው ትልቅ በመኾኑ በጥናት በታገዘ መልኩ መጠቀም እና ለትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ ስለመኾኑም አመላክተዋል፡፡
ትውልዱ ለውጭ ባሕል ከመገዛት እና ተጽዕኖ ውስጥ ከመውደቅ ይልቅ ለባሕላዊ እሴቶቹ ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባልም ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል የፎክሎር መምህርቷ ዶክተር ድርቧ፡፡
ባሕላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች መቻቻልን እና አብሮነትን ለመገንባት በአግባቡ መጠቀም እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ማሻገር ይገባል ሲሉ ዶክተር ድርቧ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- መልሰው ቸርነት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!