
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተያዘው በጀት ዓመት በጎንደር ከተማ አሥተዳደር 203 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መውሰዳቸውን ከተማ አሥተዳደሩ ገልጿል። ባለሃብቶች ከ83 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ናቸው።
ባለሃብቶች ወደ ተሟላ ሥራ ሲገቡ ለ75 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተገልጿል። በፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ.ር) የተመራው የልዑካን ቡድን በጎንደር ከተማ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በትናንትናው ዕለት ጎብኝቷል።
ልዑኩ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች፣ የሌማት ትሩፋት እና ሌሎች ልማቶችን ተዘዋውሮ የመስክ ምልከታ አድርጓል። የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ.ር) በከተማው እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል።
ቡድኑ የፖለቲካ፣ የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር እቅዶች አፈጻጸም የገመገመ መኾኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ያሉትን ክፍተቶች በመገምገም ለማስተካከል ቀጣይነት ያለው ሥራ በእቅድ ተይዞ እንደሚሠራ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ እንደተናገሩት በኢንቨስትመንት እና በሌማት ትሩፋት ዘርፍ ከተማ አሥተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
በ8 ወራት ውስጥ ከ83 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል ። 6 ፕሮጀክቶች ግንባታቸውን አጠናቅቀው ማሽን ተከላ ላይ መኾናቸውን የገለጹት ከንቲባው በቀጣይ በኢንቨስትመንት ለሚሠማሩ ባለሃብቶች 400 ሄክታር መሬት ተለይቶ የተዘጋጀ መኾኑን ገልጸዋል።
ለሥራ እድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የሌማት ትሩፋት ዘርፍ ወሳኝ መኾኑን ከንቲባው ገልጸዋል። የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ከተማ አሥተዳደሩ 20 ሚሊዮን ብር በመመደብ በአካባቢው የሚገኙ የግብርና ምርቶችን በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት እየቀረበ መኾኑን አቶ ባዩህ አመላክተዋል።
የቀዳማዊት ዝናሽ ታያቸው የዳቦ እና የዱቄት ፋብሪካ በከተማው የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ድርሻው የጎላ መኾኑን የጠቆሙት አቶ ባዩህ የስንዴ እጥረት እንዳይኖር ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጋር በመነጋገር ስንዴ እንዲቀርብ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማይ ልጃለም፤ በ8 ወራት ውስጥ ከ83 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 203 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ባለሃብቶቹ ወደ ሙሉ ሥራ ሲገቡ ለ75 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ አቶ ግርማይ ገልጸዋል። ዘገባው የጎንደር ከተማ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!