
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከፌዴራል መንግሥት ወደ አማራ ክልል የመጡ የሱፐርቪዥን ቡድን አባላት በክልሉ ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በተለያዩ ከተሞች በመገኘት እየተመለከቱ ይገኛሉ።
በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ የሱፐርቪዥን ቡድን አባላትም በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙ መሰረተ ልማቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። የሱፐርቪዥን ቡድኑ በኢፌዴሪ ከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ የሚመራ ሲኾን በከተማዋ ውስጥ የሚገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶችን፣ ዘመናዊውን እና ግዙፉን የዓባይ ድልድይ እና ሌሎችንም የልማት ሥራዎች እየተመለከቱ ነው።
የኢፌዴሪ ከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በመገንባት ላይ የሚገኙ የመንገድ መሠረተ ልማቶች የከተማዋን ውበት እና የወደፊት እድገት የሚመጥኑ መኾናቸውን ገልጸዋል። መንገዶቹ ራሱን የቻለ የብስክሌት መተላለፊያ የተሠራላቸው ናቸው፤ ይህም የከተማዋን ነዋሪዎች የብስክሌት ትራንስፖርት ተጠቃሚነት ልምድ ያገናዘበ ነው ብለዋል። በከተማዋ የሚገነቡ የሕዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት ለመገንባት ሰላም ወሳኝ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ባሕር ዳር ከተማን ዘመናዊ፣ መሰረተ ልማት የተሟላላት እና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት አድንቀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማዋ በ40 ሜትር ስፋት እና በዘመናዊ አሠራር የሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በጥሩ ኹኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። አዳዲስ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችም ጨረታቸው አልቆ በቅርብ እንደሚጀመሩ ጠቅሰዋል።
ከንቲባ ጎሹ በከተማ አሥተዳደሩ ከመንገድ ግንባታ በተጨማሪ የከተማ ውበት፣ አረንጓዴ ልማት፣ የመንገድ ዳር ሶላር መብራት ገጠማ እና ሌሎች ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
“አሁን ላይ ከተማዋ ሰላማዊ ናት ለሕዝብ የሚመቹ መሰረተ ልማቶችንም እየገነባን ነው” ሲሉም ገልጸዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች ሰላም እና ልማት ወዳድ ናቸው፤ ለሚገነቡ መሰረተ ልማቶችም አጋዥ ኾነው አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እያደረጉ ነው ብለዋል ከንቲባው።
የፌዴራል መንግሥትም በከተማዋ ውስጥ ዘመናዊውን የዓባይ ድልድይ ጨምሮ ሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለባሕር ዳር ከተማ ውበት የበኩሉን እየተወጣ ስለመኾኑ ከንቲባው ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!