
ባሕር ዳር፡ የካቲት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የምሁራን መማክርት ጉባኤው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ አስፈላጊውን ሙያዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት ላይ የአሜሪካ እና የግብጽ መንግሥታት እያራመዱት ያለውን ተቀባይነት የሌለው አቋም በተመለከተ በአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ጉባኤ የተሰጠ መግለጫ፡፡
በዝባዥ እና አረመኔ የሆነው የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት በዓለማችን ከተወገደ በኋላ ባለው የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆ መሠረት የሀገራት የሉዓላዊነት መገለጫ ከሆነው አንዱ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ጨምሮ በግዛታቸው የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ያለምንም የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት ለሀገራቸው ልማት እና ብልጽግና ማዋላቸው ነው፡፡ ይህ በግዛታቸው የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመጠቀም መብት የቅኝ ግዛት ሥርዓት ያከተመ መሆኑን እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብቶቻቸው ላይ ቋሚ የሆነ ሉዓላዊነት ያላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ይህ ደግሞ ሀገራት ፈርመው ባጸደቋቸው የተባበሩት መንግሥታት ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ቃል-ኪዳኖች፣ በአፍሪካ ኅብረት የሰዎች እና የሕዝቦች መብት ‹ቻርተር› ዕውቅና የተሰጠው ነው፡፡
በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በ1962 (እ.ኤ.አ) በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የሚኖርን ቋሚ ሉዓላዊነት (Permanent sovereignty over natural resources) በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ሀገራት በተፈጥሮ ሀብታቸው ላይ ያላቸውን ቋሚ የሉዓላዊነት መብት መጣስ የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር መንፈስ እና መርሆችን የሚጥስ ከመሆኑም በላይ ዓለም አቀፍ ትብብር እንዳይጎለብት እና ዓለም አቀፍ ሠላም እንዳይኖር ያደርጋል ሲል መግለጹ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች እና በተፋጥሮ ሀብቶቿ ላይ ያላትን ቋሚ የሉዓላዊነት መብት አሳልፈ ሰጥታ የማታውቅ ሀገር ናት።
በእርግጥ አቅም እና ሁኔታዎች አልፈቅድ ብለው እስካሁን ድረስ የተፈጥሮ ሀብቶቿን በተገቢው መንገድ አልምታ ሕዝቦቿን ከድህነት አውጥታ ራሷን ከበለጸጉት ሀገራት ተርታ ሳታሰልፍ ቀርታለች፡፡ ድህነትን አጥፍቶ ከበለጸጉት ሀገራት ጎን ለመሰለፍ ተፈጥሮ የለገሰቻትን ሀብቶቿን ዘላቂ ልማትን በሚያረጋግጥ መልኩ መጠቀም ይኖርባታል። ውስጣዊ አቅሙ እና ችሎታው እስካለ ድረስ ይህን ለማድረግ የማንም ይሁንታ እና ፈቃድ አያስፈልጋትም።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታም በዚሁ እሳቤ የተቃኘ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ግድቡን በሥራ ላይ በማዋል በዓባይ ላይ ያላትን ፍትሐዊ ድርሻ መጠቀሟ ግብጽን ጨምሮ በታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉዳት የማያደርስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያስገኝ ይታወቃል። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ በመነቃነቅ ከጉሮሮው ቀንሶ የቻለውን ሁሉ ለግንባታው ያዋጣው እና እያዋጣ የሚገኘው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ደረጃ መነቃነቁ ግድቡ በዓባይ ላይ የሉዓላዊነት መብት የሚረጋግጥለት ከመሆኑም በላይ ግድቡ ተጠናቅቆ ሥራ ላይ ሲውል ኢትዮጵያን ከድህነት በማውጣት የተሻሻለ የኑሮ ደረጃ በማረጋገጥ ረገድ የሚኖረውን የጎላ አስተዋጽኦ በውል በመረዳቱ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ ከወራት በፊት በግብጽ ጠያቂነት በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት የታላቁን ሕዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል አስመልክቶ ተጀምሮ የነበረውን ድርድር ተከትሎ በአሜሪካ እና በግብጽ የተራመደው አቋም ከላይ የሰፈረውን የሚቃረን እና ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ሆኖ አግኝተነዋል። ምንም እንኳን አለመግባባቶችን በውይይት እና በድርድር መፍታት ተገቢ ቢሆንም የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ግንባታና የውኃ አሞላል እንዴት ማከናወን እንዳለባት የዓለም አቀፍ መርሆችን ተከትላ መወሰን ያለባት ኢትዮጵያ መሆኗ እየታወቀ ከዚህ በተቃራኒ የግብጽን ኢ-ፍትሐዊ ፍላጎት ብቻ ታሳቢ ያደረግ የውኃ አሞላል ሂደት እና ጊዜ ያስቀመጠ ስምምነት ‹‹ኢትዮጵያ ልትፈርም ይገባል›› መባሉ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ያላትን ቋሚ ሉዓላዊ መብት የሚጥስ ከመሆኑም በላይ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስሜት ያለበት፣ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መንፈስን እና መርሆችን የሚቃረን፣ ዓለማቀፍ ትብብርን የማያጎለብት እና በቀጣናው ባሉ ሀገራት መካከል ያለው ሠላማዊ ግንኙነት እንዲሻክር በር የሚከፍት መሆኑን ተገንዝበናል።
በተጨማሪም የዐረብ ሊግ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ግብጽን በጭፍን በመደገፍ ያወጣው ፍርደ ገምድል መግለጫ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ መብት እና ሉዓላዊነት የሚጋፋ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ስለሆነም አሜሪካም ሆነ ግብጽ እንዲሁም የዐረብ ሊግ ፍጹም ተቀባይነት የሌለውን ኢ-ፍትሐዊ አቋማቸውን ሊያርሙ ይገባል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሁለቱ ሀገራት እና የዐረብ ሊግ እያራመዱ ያሉትን የቅኝ ግዛት መንፈስ የተጠናወተው አቋም እንዲያወግዝ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ጠንካራ የዲፕሎማሲ አቅም የሚጠይቅ መሆኑን ተረድቶ ተቀባይነት የሌለውን የሁለቱን ሀገራት አቋም ለማስቀየር የተደራጀ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ትግል እንዲያደረግ በአጽንኦት እያሳሰብን የምሁራን መማክርት ጉባኤው አስፈላጊውን ሙያዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን እንገልጻለን።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጫፍ ከጫፍ በመነቃነቅ በራሱ ገንዘብ እና አስተዋይጽኦ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሁን እስካለበት ደረጃ ማድረስ መቻሉ እጅግ የሚያስመሠግነው መሆኑን እየገለጽን ግድቡን አጠናቅቆ ሥራ ላይ የማዋል ጉዳይ ብሔራዊ ክብርን የማስጠበቅ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ግድቡ ተጠናቅቆ ሥራ ላይ እስኪውል ድረስ እንደተለመደው አስፈላጊውን አስተዋጽኦ እና ድጋፍ በማድረግ እንዲረባረብ በአክብሮት ጥሪያችን እናቀርባለን።
የካቲት 27 2012
በአማራ ክልል የምሁራን መማክርት ጉባኤ