
እንጅባራ: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በወቅታዊ የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ላይ የሚመክር የመሪዎች መድረክ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ እንጅባራ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
መድረኩ ባለፉት ወራት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተሠሩ የሰላም፣ የመልካም አሥተዳደር እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ያሉበትን ቁመና መገምገም እና ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማድረግ ላይ ያለመ መኾኑን በብልጽግና ፓርቲ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓለሙ ሰውነት ገልጸዋል።
ከሕግ ማስከበር ጎን ለጎን በክልሉ ብሎም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር የተጓተቱ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል በቀሪ ጊዜያት ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መኾኑንም አቶ ዓለሙ ተናግረዋል።
ብሔረሰብ አሥተዳደሩን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ የኅብረተሰቡን ፍላጎት በውል መረዳት እና በጊዜ ቅደም ተከተል ምላሽ መስጠት የመሪዎቹ ተቀዳሚ አጀንዳ ሊኾን ይገባልም ነው ያሉት።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የፀጥታ እና የፖለቲካ መሪዎችን ቅንጅታዊ አሠራር በማጠናከር ብሔረሰብ አሥተዳደሩን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚሁ መድረክ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከተለያዩ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ የፀጥታ እና የፖለቲካ መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
