በጎንደር ከተማ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች አፈጻጸም ዙሪያ ምክክር ተካሄደ።

13

ጎንደር: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ.ር) የተመራ የፌዴራል የሱፐርቪዥን ልዑክ ጎንደር ከተማ ተገኝቶ ባለፉት ወራቶች የተከናወኑ የሰላም እና የፀጥታ፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ እንዲሁም የመስክ ምልከታ አካሂዷል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ በበጀት ዓመቱ በከተማዋ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በሌማት ትሩፋት ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከወናቸውን አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ በከተማዋ በጀት የሚሰሩ 80 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከፕሮጀክቶቹ መካከል 21 በመቶ የሚኾኑት መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። 15 ፕሮጀክቶች ደግሞ 90 በመቶ በላይ መድረሳቸውን እንዲሁም ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ስምንት ፕሮጀክቶች መኖራቸው አንስተዋል። በከተማዋ የጠጠር መንገዶችን ጨምሮ የቄራ ግንባታዎች መካተታቸውን አያይዘውም ገልጸዋል።

ገቢ ከማሰባሰብ አኳያ ደግሞ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል። በሌማት ትሩፋት ሥራዎች በዶሮ እርባታ እና በዓሣ ሃብት ልማት ሥራዎች በርካቶች ተጠቃሚ ስለመኾናቸው አቶ ባዩህ ተናግረዋል። የመስክ ምልከታው ችግሮችን ለመቅረፍ እና ለቀጣይ ሥራዎች ውጤታማነት የሚያስችል ነው ሲሉ አንስተዋል።

የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ.ር) የተለያዩ ምልከታዎችን ማካሄዳቸውን አንስተው ጉብኝቱ በከተማዋ እየተከወኑ ያሉ ተግባራት ከእቅድ አኳያ ያሉበትን ሁኔታ በመመልከት ክትትል እና ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ስለመኾኑ አብራርተዋል።

በውይይት እና በመስክ ምልከታ የተነሱ እና የታዩ ጉድለቶችን በመያዝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን ለመፍታት እንደሚሠራም ተናግረዋል።የገጠሙ የሰላም እና የፀጥታ ችግሮችን ተቋቁሞ በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

በመድረኩ ቅርስ ጥበቃ እና ጥገና፣ ከአዘዞ ብልኮ ያለው መንገድ አለመጠናቀቅ፣ የመገጭ ፕሮጀክት መዘግየት እና ሌሎችም በማኅበረሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተጠይቋል።

ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሸዋ ኮማንድፖስት በሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ የተከናወኑ ዓበይት ተግባራትን እየገመገመ ነው።
Next articleየፀጥታ እና የፖለቲካ አመራሮችን ቅንጅታዊ አሠራር በማጠናከር ብሔረሰብ አሥተዳደሩን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ እየሠራ መኾኑን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።