የዲዛይን ቁጥጥር እና ክትትል ሥራዎች በተቀናጀ መንገድ በመሥራት የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና ገንዘብ እንዲጠናቀቁ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።

13

ደብረ ብርሃን: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የዲዛይን ቁጥጥር እና ክትትል ሥራዎች በተቀናጀ መንገድ በመሥራት የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና ገንዘብ እንዲጠናቀቁ መሥራት እንደሚያስፈልግ የሰሜን ሸዋ ዞን መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት መምሪያ አስታውቋል።

ዞኑ ከፍተኛ በመስኖ የመልማት አቅም ያለው ሲሆን ይህንን ወደ ልማት ለመቀየር ከ8 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የተመደበላቸው 20 ነባር የመስኖ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መኾናቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች መምሪያ ኀላፊ ችሮታው አስፋው ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በኢንተርፕራይዞች፣ በኮንትራክተሮች እና በክልሉ በሚገኙ የልማት ድርጅቶች እየተገነቡ ይገኛሉ። ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁም ከ2 ሺህ 780 ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 3 ሺህ 760 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረጋል ተብሏል።

በተጠናቀቀው 7 ወር ውስጥ ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት 418 ሄክታር የሚያለማ እና 1 ሺህ 254 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ የሚያደርጉ 7 ፕሮጀክቶች ግንባታቸው መጠናቀቃቸውን አቶ ችሮታው ተናግረዋል።

አንዳንድ የመስኖ ፕሮጀክቶች የተሻለ አፈጻጸም ቢኖራቸውም ትላልቅ ፕሮጀክቶች አንደ ማፈዘዝ፣ አጃና፣ ሮቢት፣ ከሰም እና ፀርጸ ወልድ የመስኖ ፕሮጀክቶች በፀጥታ እና ከዲዛይን ችግር ጋር በተያየዘ በበጀት ዓመቱ ወደሥራ አለመገባቱን ነግረውናል።

ከጀማ ፈዘዝ ውጪ ያሉት ትላልቅ ፕሮጀክቶች በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩ መግባባት ላይ መደረሱን የነገሩን አቶ ችሮታው ጀማ ፈዘዝ የዲዛይን ማሻሻያው ተጠናቅቆ በቀጣዩ በጀት ዓመት ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል።

የዲዛይን ቁጥጥር እና የክትትል ሥራዎች በተቀናጀ መንገድ በመሥራት የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና ገንዘብ እንዲጠናቀቁ እየሠሩ እንደሚገኙም ኀላፊው አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- ገንዘብ ታደሰ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጎጃምን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ቁርጠኛ ኾነው ወደ ሥራ እንደሚገቡ የጎጃም ኮማንድፖስት አመራሮች አረጋገጡ፡፡
Next articleየሸዋ ኮማንድፖስት በሰላም እና ጸጥታ ዙሪያ የተከናወኑ ዓበይት ተግባራትን እየገመገመ ነው።