የጎጃምን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ቁርጠኛ ኾነው ወደ ሥራ እንደሚገቡ የጎጃም ኮማንድፖስት አመራሮች አረጋገጡ፡፡

23

ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከሁሉም የጎጃም ዞኖች ከመጡ ከወረዳ አመራር በላይ ኀላፊነት ያላቸው 400 አመራሮች በቀጣይ በሚያከናውኑት የፀጥታ ሥራ ላይ በባሕር ዳር መክረዋል።

በኮማንድፖስቱ ቀጣና የሚከናወኑ ተግባራቶች፣ የወታደራዊ ስምሪት እና የሕዝብ ማደራጀት እንቅስቃሴ፣ የክልሉን የፀጥታ ኃይል አደራጅቶ ወደ ሥራ የማስገባት ሥራዎች እንዲሁም ጽንፈኛውን የገባበት ገብቶ በማደን ለሕግ የማቅረብ ግዳጆች በሚመሩበት ዕቅድ ላይ አመራሮቹ ተወያይተዋል፡፡

የጎጃም ኮማንድፖስት ሰብሳቢ እና የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል መሐመድ ተሰማ የመሩት ይኽ መድረክ እንደ ክልል የታዩ ጥንካሬዎችን የሚያጎለብቱ በኮማንድፖስቱ ያለውንም ክፍተት የሚሞሉ እንዲሁም ጎጃምን ከችግር የሚያወጡ አስተሳሰቦችን ፈጥሯል፡፡

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) እንደተናገሩት አመራሩ የአማራ ክልልን ከጽንፈኛው አጽድቶ ነጻ ማውጣት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ብርጋዲየር ጀኔራል መለስ መንግሥቴ የኮር አዛዥ እና የምዕራብ ጎጃም ዞን ኮማንድፖስት ሰብሳቢ፣ ብርጋዲየር ጀኔራል አዘዘው መኮንን የኮር አዛዥ እና የምስራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድፖስት ሰብሳቢ፣ የኮር አዛዥ እና የሰሜን ጎጃም ዞን እና የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኮማንድፖስት ሰብሳቢ ብርጋዲየር ጀኔራል አዲሱ መሀመድ እንደተናገሩት ጽንፈኛው በየሥርቻው ተሸጉጦ ስለሚገኝ አሁንም የክልሉን የፀጥታ ኃይል በማደራጀት የገባበት በመግባት ከጎጃም ማጽዳት አለብን ነው ያሉት።

የምስራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሀኑ እና የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ በሰጡት ሃሳብ ጽንፈኛውን የሚጠላ እና በድፍረት ታግሎ አካባቢውን ወደ አንጻራዊ ሰላም የሚመልስ ማኅበረሰብ መፍጠር አለብን ብለዋል፡፡

ውይይቱ በጎጃም ኮማንድፖስት በወጣው እቅድ መሠረት በቀጣናው የሚካሄደውን ጽንፈኛውን በያለበት አሳዶ፣ አድኖ እና ከቦ የማጽዳት ኦፕሬሽን ሁሉም አመራር የየራሱን የኀላፊነት ድርሻ በመወጣት የጎጃምን ሰላም ለማስፈን የጋራ መግባባት እና አንድነት ፈጥሯል ማለቱን ከመከላከያ ሰራዊት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ከስዊዘርላንድ ጋር ያላት ግንኙነት ታሪካዊ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አጽቀሥላሴ
Next articleየዲዛይን ቁጥጥር እና ክትትል ሥራዎች በተቀናጀ መንገድ በመሥራት የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና ገንዘብ እንዲጠናቀቁ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ።