
አዲስ አበባ: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የስዊዘርላንድ መንግሥት በአዲስ አበባ ለሚያስገነባው አዲስ የኢምባሲ ሕንፃ የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በጋራ በመኾን የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
የሚገነባው ሕንፃ 40 የሚኾኑ የመስሪያ ቢሮዎችን እና ሁነቶችን የሚፈጥር ሲኾን ሁለት ዓመት የግንባታ ጊዜ ተይዞለታል። በሀገር ውስጥ የግንባታ ግብዓቶች እንደሚገነባም ተገልጿል።
በመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አጽቀሥላሴ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት እሚያምነው ከስዊዘርላንድ ጋር ጠንካራ እና ታሪካዊ ግንኙነት አንዳለው ነው።
ግንኙነቱ በቴክኖሎጂ፣ በግንባታ እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ጠንካራ ግንኙነት አላቸው ብለዋል። ስዊዘርላንዳዊው ኤልፈርድ ኤልግን በምሳሌነት ያነሱት ሚኒስትሩ በቤተ መንግሥት፣ በባቡር፣ በድልድይ እና መንገድ ግንባታዎች እጃቸው አንደነበረበት ጠቅሰዋል፡፡ ይኽም የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ጠንካራ ለመኾኑ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የኢምባሲው የአርክቴክቸር ግንባታ ዲዛይን ከሸሆጀሌ ቤተመንግሥት ቅርጽ በመወሰዱም ሚኒስትሩ አድንቀዋል። የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናሲዎስ ካሲስ ዛሬ እዚህ የኾነው በአጋጣሚ ሳይኾን ባለ ጠንካራ ግንኙነት ላይ መሠረት ተደርጎ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
ግንባታውም ጠንካራውን ግንኙነት ማጠናከሪያ ሁነት ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በግንባታው ውስጥ ግንኙነቱ አብሮ ይገነባል ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!