
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከፍተኛ እጣንና ሙጫ ዛፍ ካለባቸው አካባቢዎች ምዕራብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። ዞኑ ካለው 760 ሺህ ሄክታር የደን ሽፋን ውስጥ 30 በመቶው የሚኾነው በነጩ ወርቅ የእጣን ዛፍ የተሸፈነ እንደኾነ ይነገራል። ታዲያ ይህ ተፈጥሮ የለገሰችው ነጭ ወርቅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሥራ እድል መፍጠሪያነት እየዋለ ቢገኝም ክልሉ ካለው አቅም አኳያ ሲታይ የተሰጠው ትኩረት ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
በዞኑ በእጣን እና ሙጫ ማምረት ላይ እንደሚገኙ የነገሩን መሰረት ማሞ እንዳሉት ከሀብቱ የሚገኘው ገቢ በአካባቢው ከሚመረቱ ገበያ ተኮር ሰብሎች ከሚገኘው ገቢ ከእጥፍ በላይ ብልጫ አለው። “በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” እንደሚባለው ከፍተኛ የሀብቱ ክምችት በሚገኝበት አካባቢ እየኖሩ አንድም ቀን እንኳ ወደ ሀብት ማማ እንደሚያሸጋግር አስበውት አያውቁም። ይሁን እንጂ በ2014 ዓ.ም በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች ለኩንታል እስከ 23 ሺህ ብር ግብይት ሲፈጽሙ የተመለከቱት ወይዘሪት መሰረት በ2015 ዓ.ም በማኅበር በመደራጀት ወደ ማምረት እንደገቡ ነግረውናል። ከምርቱ በተገኘው ገቢ ከእጣንና ሙጫ ማምረት በተጓዳኝ በፍየል እርባታ ሥራ ጭምር ተሠማርተውም ይገኛሉ።
በመተማ ወረዳ ሻሽጌ ቀበሌ የንጋት ተፈጥሮ ሀብት ልማት ማኅበር አባል የኾኑት ፈለቀ ሲሳይ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በእጣን እና ሙጫ ምርት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
ማኅበሩ 167 አባላት እንዳሉት ያነሱት አምራቹ በ26 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዓመት እስከ 150 ሺህ ብር በነፍስ ወከፍ ገቢ እንደሚያገኙም ነው የነገሩን። ባለፉት ሦስት ዓመታት ከእጣን እና ሙጫ ምርት ባገኙት ገቢ የከተማ ቦታ መግዛታቸውን እና የቁም እንስሳትን እያረቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል። ይሁን እንጅ የሕገ ወጥ አምራቾች መበራከት በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩ ማኅበራትን እየተሻሙ ይገኛሉ፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን የደን እና ዱር እንስሳት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደግነት አበበ ለአሚኮ እንዳሉት በ2015 ዓ.ም ከ5 ሺህ ኩንታል በላይ እጣን እና ሙጫ ማምረት ተችሏል፤ ከ92 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር በላይ ገቢም ተገኝቷል፤ 18 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር ደግሞ ለመንግሥት ሮያሊቲ ክፍያ ገቢ ተደርጓል።
በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ከ9 ሺህ 400 በላይ ኩንታል እጣን እና ሙጫ በማምረት ከ219 ሚሊዮን በላይ ብር ገቢ ለማግኘት እየተሠራ ይገኛል፡፡ 58 ሚሊዮን ብር የሮያሊቲ ክፍያ ለመንግሥት ገቢ ለማድረግም ታቅዷል፡፡ ለዚህ ደግሞ 27 በተፈጥሮ ሀብት የተደራጁ ማኅበራት እና 15 ባለሀብቶች የእጣን እና ሙጫ ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ለ2 ሺህ 911 ወጣቶች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
ዘርፉ ገና ያልተነካ፣ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር የሚችል እና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ሀብት መኾኑን ያነሱት ኀላፊው በቀጣይ ለወጣቶች ሥልጠናዎችን በተደራጀ መንገድ ለመስጠት፣ ምርቱ ጥራት ባለው መንገድ እንዲመረት ቴክኖሎጂ ማቅረብ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ እንዲቻል እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት በዞኑ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሕገ ወጥ መንገድ ሲካሄድ የነበረውን የማምረት ሥራ ለመከላከል ክትትል እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች እና የተደራጁ ወጣቶችም እንዲያመርቱ የተረከቡትን አካባቢ ለሕገወጦች አሳልፎ ከመስጠት ተቆጥበው አካባቢያቸውን በመጠበቅ እንዲያመርቱ አሳስበዋል።
ምዕራብ ጎንደር ዞን ከ234 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በእጣን እና ሙጫ ደን የተሸፈነ ነው፤ ይህ ሀብት ደግሞ 21 ሺህ ኩንታል ምርት የማምረት አቅም አለው። ይህ ሀብት አሁን ባለው ዋጋ እንኳ ለገበያ ቢቀርብ 609 ሚሊዮን ብር ገቢ ማስገኘት ይችላል። ከዚህም ባለፈ 121 ሚሊዮን 800 ብር ለመንግሥት ገቢ የማስገኘት ሙሉ አቅም እንዳለው ከዞኑ የደን እና ዱር እንስሳት ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!