
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ከተጀመሩ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩት የአዘዞ ብልኮ መንገድ ፕሮጀክት እና የመገጭ ግድብ ፕሮጀክቶች በኅብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታ እያስነሱ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ.ር) የተመራ የፌዴራል መንግሥት የሱፐርቪዥን ልዑክ ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
የሱፐርቪዥን ግምገማው ዓላማ ድጋፍ የሚፈልጉ እና ማነቆ የኾኑ ጉዳዮችን ለመለየት፣ በአንድ ላይ በመሰብሰብ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ግብዓት እንደሚኾን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የፌዴራል መንግሥት የሱፐርቪዥን ልዑክ በግብርና ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎችን በወለቃ የሚገኘውን ስድስት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ተመልክቷል። የችግኝ ጣቢያዎች ካለው የፀጥታ ሁኔታ አኳያ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች መኾናቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የፌደራል መንግሥት ያሉትን ክፍተቶች በመገምገም ለማስተካከል በእቅድ ተይዞ እንደሚሠራ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ እንደገለጹት የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በተደራጀ መንገድ የመቀልበስ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
ሕዝባችን በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ከንቲባው ገልጸዋል። በከተማ ደረጃ እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም የተሻለ መኾኑን የገለጹት ከንቲባው በፌዴራል መንግሥት እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች ግን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ አለመቻሉን ጠቁመዋል።
የአዘዞ ብልኮ መንገድ እና የመገጭ ግድብ ፕሮጀክቶች ባለመጠናቀቃቸው በተለያዩ ጊዜ በሕዝብ ቅሬታ እየተነሳባቸው መኾኑን አቶ ባዩህ በውይይቱ አንስተዋል። የጎንደር ከተማ ትምህርት ቤቶች በርካቶቹ ከደረጃ በታች በመኾናቸው የገለጹት ከንቲባው ደረጃቸውን ለማሻሻል የፌዴራል መንግሥት እገዛ እንዲያደረግ ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!