
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራ እና ሰው ሠራሽ ደን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አበሩ ጠና በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት እስካሁን ለአረንጓዴ አሻራ ልማት አምስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል።
ከእነዚህም ውስጥ የደን ችግኝ ሁለት ቢሊዮን እንዲሁም የቀርከሃ 60 ሚሊዮን የሚይዝ ሲሆን ቀሪው “የአግሮ ፎረስተሪ” ችግኞች ናቸው። ለተከላ የተዘጋጁ ችግኞች ተብለው የሚለዩት ከሃያ አምስት ሴንቲ ሜትር በላይ ቁመት እና ሊጸድቁ የሚችሉ መኾናቸውንም አብራርተዋል።
በአጠቃላይ በ2016 ዓ.ም ለሚካሄደው የሁለተኛ ምዕራፍ ሁለተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች ለማዘጋጀት እቅድ ተይዟል ሲሉ ገልጸዋል። ቀሪው አንድ ቢሊዮን በአጭር ጊዜ ሊደርሱ የሚችሉት ችግኞች የሚዘጋጁበት ይሆናል ብለዋል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ልማት እንቅስቃሴ ካሉት 99 ሺህ 810 ችግኝ ጣቢያዎች ለ61 ሺህ 810 ካርታ የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል አቶ አበሩ። ይህም የት እንዳሉ፣ ምን ያህል እያመረቱ እንደኾነ እና የዝግጅት አካሄዳቸውንም በቅርበት ለመቆጣጠር እንዲሁም በቋሚነት ለችግኝ ማፍያ የሚያገለግሉትን እና እንደ አዲስ ወደ ችግኝ ማምረት እየገቡ ያሉትን ለመለየት የሚያስችል ይኾናል ብለዋል።
በተጨማሪም ዘንድሮ ከእስካሁኑ በተለየ ከችግኝ ማዘጋጀት በተጓዳኝ 700 ሺህ ሄክታር መሬት የመትከያ ቦታ ልየታ የሚሠራ እንደኾነ ጠቁመዋል። ለዚህም እስካሁን 400 ሺህ 899 ሄክታር መሬት መለየቱን እና ለ289 ሺህ 869 ሄክታር ካርታ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። የቀረውም በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት የሚጠናቀቅ ይሆናል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!