
ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ወይዘሮ ቅድስት ሐይሌ እና አቶ ቢኒያም ክፍሌ ላለፉት 12 ዓመታት የትዳር ሕይዎታቸው ያማረ እና የሠመረም ነበር፡፡ በዚህ አርአያ በኾነ ትዳር ውስጥ ከሃብት እና ንብረት በተጨማሪ ልጆችንም አፍርተውበታል፡፡
የሁለቱ ጥንዶች ትዳር ከጊዜ ወደ ጊዜ ንፋስ እየገባው እና አለመግባባቶች እያየሉ መጥተው ወይዘሮ ቅድስት ከቤታቸው ይወጣሉ፡፡ “ሽማግሌ አያጠፋ” እንዲሉ መልሰው ደግሞ በአሸማጋዮች አማካኝነት ይገባሉ፡፡
እንዲህ እያለ የቀጠለው ትዳር ቋሚ ምሰሶዎቹ ተናግተዋል እና አሁንም አለመግባባቶች አይለው ሚስት ትቀርበኛለች ወዳለቻት ጓደኛዋ ደውላ እሷ ቤት እንደምታርፍ ትነግራታለች፡፡
ጓደኛዋ ወይዘሪት ጌጤ አመራም እንግዳ ሲመጣ ያውም ጓደኛ አይከለከልም እና በቤቷ ታሳርፋታለች፡፡
ጓደኛሞች ስለጉዳዩ ያነሳሉ ይጥላሉ። የትዳር ጓደኛዋ ባሕሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመምጣቱ ጥላ ለመውጣት ስለመገደዷ ትነግራታለች፡፡ ጓደኛዋም በይ እስኪ ኩርፊያችሁ እስኪበርድ ተቀመጭ ብላ ለአንድ ሳምንት ያክል በቤቷ አስጠለለቻት፡፡
በዚህ ድርጊት የተበሳጨው ባል ወደ ወይዘሪት ጌጤ አመራ ቤት በመሄድ “ባለቤቴ ቤቷን ጥላ እንድትወጣ እየገፋፋሻት ያለሽ አንች ነሽ” በማለት ይነጋገራሉ፡፡ ወይዘሪት ጌጤም ባጎረስኩ እና ደግ ባደረኩ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ንግግር ትናገራለህ በሚል ተነጋግረው ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ ባል አቶ ቢኒያም ክፍሌም በነገሩ ተበሳጭቶ ፍርድ ቤት እንደሚያቆማት ከነገራት በኋላ ይለያያሉ፡፡
ከሁለት ቀናት በኋላ እንደዛተው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰደው፡፡ ፍርድ ቤቱም ለወይዘሪት ጌጤ አመራ የክስ መጥሪያ ይልካል፡፡ መጥሪያው የደረሳቸው ወይዘሪት ጌጤ አመራ ፍርድ ቤቱ ባስቻለው ችሎት ከሁለቱም ወገን የቀረበውን የክስ ፍሬ ነገር ከመረመረ በኋላ ወይዘሪት ጌጤ ጥፋተኛ ናቸው ብሏቸዋል፡፡
ለመኾኑ ይህ ድርጊት እንዴት ወይዘሪት ጌጤን ጥፋተኛ ሊያስብል ቻለ? በማለት የሕግ አማካሪውን እና ጠበቃ እስመለዓለም ምህረት ጠይቀናቸዋል። አማካሪና እና ጠበቃ እስመለዓለም በፍታ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2050 በግልጽ እንደተደነገገው አንድን ትዳር በጓደኛም፣ በቅርብ ሰው፣ አለያም በዘመድ ትዳሩ እንዲፈርስ መገፋፋት፣ ይህ ትዳር ድሮም ቢኾን እንደማይኾን አውቅ ነበር በማለት የገፋፋ እና ትዳሩ እንዲፈርስ ያደረገ እንደኾነ በሕግ እንደሚጠየቅ አስረድተዋል፡፡
አንዳንድ ጊዜ የቅርብ የምንለውን ሰው የረዳነው መስሎን ማማከር እና ትዳሩ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ማድረግ፣ ምን ችግር አለው ትዳር ቢፈርስ ሌላ ታገቢያለሽ ወይም ታገባለህ ብሎ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ የፍትሐ ብሔር ኀላፊነት እንደሚያመጣ ነው የነገሩን፡፡
በባል እና በሚስት መካከል ግጭት እንዳለ እያወቀ ያሳደረም በሕጉ እንደሚጠየቅ ነው የነገሩን፡፡ የሕጉ ዓላማም በቤተሰብ መካከል መረጋጋት እንዲፈጠር ከሌላ ወገን ግፊት ተፈጥሮ መለያየት እንዳይኖር ለማድረግ እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡
በፍትሐ ብሔር ሕጉ 2051 ላይ በተቀመጠው ልዩ ድንጋጌ ላይ እንደተመላከተው ግጭት ውስጥ የገቡ ባልና ሚስትን አንደኛውን ወገን ወስዶ በእንግድነት ማስቀመጥ የሚቻለው ሌላኛው ወገን ጉዳት ያደርሳል ተብሎ ከታመነ ብቻ መኾኑንም ነው ያስረዱት፡፡ በመኾኑም ሰዎች ሕግን አውቀው ከሚመጣባቸው የሕግ ተጠያቂነት እንዲድኑ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!