የአካባቢውን የጸጥታ ስጋት ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገለጸ።

74

ባሕር ዳር: መጋቢት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት ወረዳ እና አካባቢው በሕዝብ ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ሲያደርስ የነበረውን የጽንፈኛ ኃይል መቆጣጠር መቻሉ ተገልጿል፡፡

አሁን ላይ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ላይ የሚገኙ የክፍለ ጦሩ የሠራዊት አባላት ግዳጃቸውን በሕዝባዊነት እና በቁርጠኝነት እየተወጡ መኾኑ ተጠቁሟል። የሻለቃው አዛዥ ሻለቃ ተስፋሁን ኮኬ የአካባቢውን የጸጥታ ስጋት ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሻለቃ ተስፋሁን ሠራዊቱ ግዳጁን እየተወጣ ያለው የየአካባቢውን ነዋሪዎች በማወያየት እንደኾነም አስገንዝበዋል፡፡ ከፀረ ሰላም ኃይሉ ጋር በጋራ ሲሠሩ የነበሩ ኃይሎችን የመለየት ተግባር በማከናወን እንዲሁም በየቀጣናዎቹ የሚሽሎኮሎኩ የጥፋት ኃይሎችን በአስተማማኝ ሁኔታ መቆጣጠር መቻሉንም አስረድተዋል።

ጽንፈኛ ኃይሉን በመቆጣጠር በርካታ ተተኳሾችን ከመማረክ በተጨማሪ ከኅብረተሰቡ ጋር በተደረጉ የማጥራት ሥራዎች በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ነው ያብራሩት።
መቶ አለቃ ተስፋየ ጫሌ ጽንፈኛ ኃይሉ የኅብረተሰቡን ሰላም በማወክ ሕዝብን ለማሰቃየት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ሠራዊቱ ተረድቶ በወሰደው የሰላም ማስከበር ሥራ የአካባቢውን ሰላም መመለስ እንደቻለ አስገንዝበዋል፡፡ ሰላምን የማረጋገጥ ሥራውንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ የትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት እንዳይኖር እየተሠራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።
Next articleምክር ቤቱ 18ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ያካሂዳል።