
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት እንዳይኖር እየተሠራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ገልጿል። ከተማ አሥተዳደሩ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ውጤታማ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ተነግሯል።
ኮሌራን ጨምሮ በንጽሕና እጦት ምክንያት ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፉ የሚችሉ የጤና ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ የጤና ችግሮች በማኅበረሰቡ ዘንድ የከፋ ችግር ከማድረሳቸው አስቀድሞ ተቋማት በዋሽ መርሐ ግብር አማካኝነት ልዩ ልዩ ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡
የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳር ጤና መምሪያ በመርሐ ግብሩ የተሠሩ ተግባራት ማኅበረሰቡን ተላላፊ ከኾኑ የጤና ችግሮች አስቀድመው ያዳነ ነው ብሏል፡፡ በመምሪያው የጽዳት እና አካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያ በየነ ሳኅሉ እንዳሉት በሆስፒታል፣ በጤና ጣቢያ እና በቀበሌ የዘርፉ ባለሙያዎች ተመድበው በግንዛቤ ፈጠራ እና በተግባር ሥራዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በተለይም ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት እንዳይኖር በመርሐ ግብሩ በመታገዝ እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል፡፡ አቶ በየነ እንዳሉት የሥነ ጤና፣ የሥነ ጽዳት እና የሥነ ውኃ /ዋሽ/ መርሐ ግብር ከፍተኛ የገንዘብ አቅምን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ በመኾኑም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በዘርፉ ያደረጉትን ቅንጅታዊ አሠራር ይበልጥ ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
ከግንዛቤ ፈጠራ ጀምሮ መሰረተ ልማት እስከማሟላት የደረሰ ተግባር ለማከናወን ቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራም ተጠቅሷል፡፡ ደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር አሁን ላይ በፈጣን እድገት ላይ ትገኛለች፡፡ የከተማዋ እድገት ከመርሐ ግብሩ አንጻር ሲቃኝ ሰዎች የግል እና የአካባቢያቸውን ንጽሕና የመጠበቅ ልምዳቸው ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት የያዘው እቅድ እንዲሳካ የነዋሪዎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉት ባለሙያው በተለይ የማኅበረሰቡ የደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ሊስተካከል እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማትም በመርሐ ግብሩ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!