“ትምህርት ቤቴ ናፈቀኝ” የሰላም እጦት ከቤት ያዋላት ተማሪ

154

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ልጆች ትምህርት ቤት ናፈቃቸው፣ አስተማሪዎቻቸውን ጋሼ እና እትዬ ማለት ራቃቸው፣ መምህራን ጠመኔ ይዘው ከተማሪዎቻቸው ፊት መቆም ብርቅ ኾነባቸው፡፡

በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት እና ከትምህርት ቤት እርቀዋል፡፡ ከመምህሮቻቸው እግር ስር ተቀምጠው፣ ዕውቀት ገብይተው ነገን የተሻለ ለማድረግ ያለሙት ሕልም ፈተና ገጥሞታል፡፡ ውሏቸው በቤት ውስጥ ተወስኗል፡፡ በቤትም ውስጥ ኾኖ ነጻነት ቢኖረው በተሻለ ነበር፡፡ በቤታቸውም ስጋት ያንዣበበት ኾነ እንጂ፡፡

በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተማሪዎችን ከትምህርት ጋር አራርቋል፡፡ ለዓመታት የደከሙ እና የተደከመባቸው ልጆች ተስፋቸው ላይ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ወላጆችም ድካማችን በባዶ ቀረ የሚል ስጋት ተደቅኖበታል፡፡

ስሟን ለደኅንነቷ ሲባል ያልገለጸችው ባለታሪካችን የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ነዋሪነቷ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ አሥተዳደር ነው፡፡ ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለመፈተን ራዕይ ሰንቃ የቆየችው ባለታሪካችን “በአካባቢው በተፈጠረው ችግር ለረጅም ወራት አልተማርንም፤ ከሰሞኑ የጸጥታው ሁኔታ ተስተካክሏል ተብሎ ትምህርት ጀምሮ ነበር፤ ትምህርት ቤት ሄደን መማር ጀምረን ተኩስ ተጀመረ፤ ተማሪዎች ተደናግጠው ወደየቤታቸው ሄዱ፡፡ የጸጥታ አስከባሪዎች ደግሞ ተረጋግታችሁ ቆዩ አሉን፡፡ በመካከል ተወዛገብን፡፡ ተኩስ ስላለ በማግሥቱ ለመሄድ ተቸገርን እና ቀረን” ነው ያለችን፡፡

ተማሪዋ ከእርሷ ጋር የሚወዳደሩትን ባሰበች ጊዜ ታዝናለች፤ ይከፋታል፡፡ የሚከፋት በእነርሱ መማር አይደለም፡፡ እርሷ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን መማር ሲገባት ሳትማር በመቅረቷ እንጂ፡፡

“ቤት በመዋሌ ከፍተኛ የሞራል ስብራት ደርሶብኛል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች እየተማሩ ነው፡፡ እኛ ከዚህ ቁጭ ብለን አሁን ይተኮስ፣ አሁን እንሞት ይኾን እያልን ተቸግረን ነው ያለነው፡፡ እኛ ላይ ያለው ተጽዕኖ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንማራለን ብለን እያሰብን ስላልኾነ አናነብም፣ ዝም ብለን ነው የምንውለው፤ መማር እንፈልጋለን፤ ትማራላችሁ ተብለን ተስፋ ተሰጥቶን ደስታችን ወሰን አልነበረውም፡፡ ግን ወዲያው ተቋረጠ፡፡ እንደተማሪ አዝኛለሁ፡፡ እያነበብኩም አይደለም፡፡ ለሕይወቴ እየፈራሁ ነው ያለሁት” ብላለች፡፡

“ተኩስ እየሰማን እንዴት ልናነብ እንችላለን? ነገስ ስለመማራችን እርግጠኞች አይደለንም፡፡ በትምህርት ጊዜ ከቤት መዋል ተስፋ እያሳጣ ነው የሚሄደው ” ነው ያለችን፡፡
የትምህርቱን ጊዜ እያነሳች ስትናገር “ትምህርት ቤቴ ናፍቆኛል” ትላለች፡፡ እርሷ ብቻ አይደለችም፤ ሌሎች ጓደኞቿም ትምህርት ቤት እንደናፈቃቸው ነው የነገረችን፡፡ “ወላጆቻችንም ስጋት ላይ ናቸው፤ አንዳንድ ወላጆች ሂዱ ወደ ትምህርት ቤት ይላሉ አንዳንዶቹ ግን በፍፁም ይላሉ፤ ምክንያቱም በመከራ ያሳደጓቸውን ልጆቻቸውን ማጣት አይፈልጉምና” ነው ያለችው፡፡

ስለቀጣዩ ጊዜ ስትናገር “ብቻ ሰላም ይሁን ሌትም ቀንም ቢኾን እንማራለን፤ ክረምትም ቢኾን እንማራለን፤ ሁሉንም እንቀበላለን፤ ቤተ መጻሕፍትም እንውላለን፤ አሁን ግን ቤተ መጻሕፍትም መሄድ የለም፤ የጸጥታ ችግር ከሌለ ያለፈውን ጊዜ እናካክሰዋለን፡፡ ብንማር ደስ ይለናል” ብላለች፡፡

ወላጆች ልጆቻቸው ወደ አልተገባ ቦታ እንዳይሄዱ ማድረግ እንደሚገባቸውም ተናግራለች፡፡ እንደ ሌሎች እኩዮቻችን በጊዜው ተምረን ቢኾን ኖሮ ጥሩ ውጤት አስመግዝበን ዩኒቨርሲቲ መግባት ነበር ዓላማችን፡፡ አሁንም ያለውን ጊዜ መጠቀም ይገባል፡፡ ሰላም እንዲኾን እና እንድንማር እንፈልጋለን ብላለች፡፡

ለመማር ማስተማሩ ፈተና የኾኑ ጉዳዮችን ስታነሳ ከኮሮና ቫይረስ ጀምሮ የትውልድ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ በኮሮና ቫይረስ ጊዜ ለበርካታ ወራት ከትምህርት ገበታ ስለወጣን ብዙ ተማሪ ውጤቱ ቀንሶበታል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የመጣው ጦርነት ጫና ፈጠረ፡፡ አሁን ያለው የሰላም ችግር ሲፈጠር ደግሞ ብዙ ተማሪ ከትምህርት ራቀ፡፡

በአማራ ክልል ከፍተኛ ውጤት ያመጣል ተብሎ የተገመተ ተማሪ ውጤቱ ተበላሽቷል፡፡ እንደተጠበቀው አልመጣም፡፡ ይሄን ያደረገው ተደራራቢው ችግር ነው፡፡ በእኔ እምነት ለብዙ ነገር የሚጠበቁ ተማሪዎች ቀርተዋል፡፡ ግጭቱ ቢቆም ውጤቱን ለማስተካከል አሁንም ቢኾን አልረፈደም” ነው ያለችው፡፡

በተደጋጋሚ በተፈጠረው እና እየተፈጠረ ባለው ችግር ሀገር የምትፈልጋቸውን እና የሚያስፈልጓትን ልጆቿን አጥታለች፡፡ በርካታ ወጣቶች ተስፋ እያጡ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሄደዋል ብላለች፡፡

በጎንደር ዪኒቨርሲቲ የሥነ- ልቦና መምህርት መቅደስ መለሰ ከኮሮና ቫይረስ ወቅት ጀምሮ ያለው ውጥረት እና የክፍል መቆራረጥ በርካቶችን ከንባብ አርቆ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡ ፍርሃት የነበረበት ወቅት ስለነበር የታሰቡ ሃሳቦችን እና እቅዶችን በሙሉ ቀይሮታል፡፡ ተማሪዎች ከክፍል መቆራረጥ በኋላ ወደ ክፍል ሲመጡ የማካካሻ ጊዜ በመኾኑ ተጣድፈው እንደሚማሩ፣ ማወቅ አለማወቃቸው እንደማይለካ እና ወደ ቀጣዩ ዙር መሻገራቸው ብቻ ትኩረት የሚደረግበት እንደነበር ነው የተናገሩት። ተማሪዎች የሚማሩበትን ዓላማ የመዘንጋት ችግር እንደገጠማቸውም ይገልጻሉ፡፡ የቆዬው ሕመም ዓላማቸውን የሚያዘናጋ ነበር ነው የሚሉት፡፡ በተለይ ለልጆች ደግሞ የከፋ ነው፡፡

ተማሪዎች በጦርነት ውስጥ የሚያዩዋቸው፣ የሚሰሟቸው፣ በማኅበራዊ ሚዲያው የሚራገበው ሁሉ ወደፊት የሚቆዩለት ነገር፣ ወደፊት የሚሠሩት ሥራ እንደሌለ እና ወደፊት የሚኖሩላት ሀገር እንደሌለች ስሜት የሚፈጥር ነበር ነው የሚሉት፡፡ በተማሪዎች ላይ የተፈጠረው ፍርሃት ወደፊት ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡ በተለይም በግጭት ውስጥ ያሉ ተማሪዎች በትምህርት ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ ሲያደርግ አይተናል ነው የሚሉት፡፡

“በግጭት ውስጥ ያሉ ተማሪዎች መማር፣ ማወቅን ሳይኾን የሚፈልጉት ማለፍን ነው፡፡ የትኛውን ሀገር ለመረከብ ነው የምማረው? እኔ ለፍቼ ምን አመጣለሁ? ብለፋ ምን ለውጥ አመጣለሁ? ከእኔ በፊት የተማሩ ልጆች ምን አገኙ? የሚል ስሜት እንዲኖራቸው አድርጓል” ነው ያሉት መምህርቷ፡፡

ተማሪዎች በግጭት ውስጥ ሲያልፉ ምን ማድረግ አለባቸው የሚለውን የሚያሳያቸው አልተገኘም፡፡ የተማሪዎችን ችግር የሚረዳ እና ለችግሮቻቸውም መፍትሔ የሚያመላክት ጥናት ያስፈልጋልም ይላሉ መምህርቷ፡፡ የኮሮና ቫይረስ እና የጦርነት መከታተል በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሰ ነውና፡፡

ተማሪዎች አሁን መማር፣ ተምሮ መለወጥ እና ነገ የተሻለ ነገር ላይ መድረስ አይደለም የሚያሳስባቸው፣ የሚያሳስባቸው በሕይወት መኖር ነው፤ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከሚዲያ የሚሰሙት ሁሉ በሕይወት መቆዬት አለመቆዬትን እንዲያስቡ እንጂ ስለ ትምህርት እንዲያስቡ አያደርጋቸውም ነው የሚሉት፡፡

ተማሪዎች ሕይወት ትርጉም አልባ የሚኾንባቸው፣ ሰላም በኾነ ጊዜ ማግኘት የሚፈልጉትን ማግኘት አለመቻላቸው መኾኑንም ያነሳሉ፡፡ አሁን ተወዳድሬ ከሌሎች ጋር እኩል መኾን አልችልም የሚል ስሜት እየተፈጠረ መኾኑን ነው የሚያነሱት፡፡ የትምህርት መዘጋት ሲያዩ ጥረታቸው ባዶ እንደኾነ፣ ጥረው የሚያመጡት ለውጥ እንደሌለው እንዲያስቡ ያደርጋል” ብለዋል፡፡

የሥነ ልቡና መምህርቷ ለችግሮች መፍትሔ ሲያመላክቱ ዓለም ከምትገባበት ቀውስ ማስቆም ባይቻልም ሰዎች ራሳቸውን ማወቅ እና መግዛት ይችላሉ ይላሉ፡፡ ለተማሪዎች ሥልጠናዎችን መስጠት፣ ራሳቸውን እንዲረዱ ማድረግ፣ ከየትኛው ሁኔታ መውጣት እንደሚቻል ማሳየት የመፍትሔ ሃሳብ ነው ይላሉ፡፡ ተማሪዎችን ሰላም እንዲመጣ እነርሱም አስተዋጽኦ እንዳላቸው መንገር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

“ሀገር እንደምትፈረስ የሚያወራ ቤተሰብ ካለ የተሻለ ትውልድ ወደፊት ማየት አይችልም፤ ችግር የሚፈታበት ጊዜ እንዳለና፣ ችግር ቋሚ እንዳልኾነ፣ መልካም የሚኾን ጊዜ እንዳለ፣ ግጭት የሕይወት አካል እንደኾነ እና ለእነርሱ ትውልድ ብቻ የመጣ እንዳልኾነ እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል” ብለዋል፡፡

ሀገር ተስፋ እንደሌላት ሲሰሙ የሚፈጠረው ተጽዕኖ ከባድ ነው፡፡ ቤተሰብ እና መምህራን ተማሪዎችን የሚያገኙበት መንገድ መታየት አለበትም ይላሉ፡፡ ተስፋ የቆረጠ እና የሚወቅሳቸው መምህር የሚያስተምራቸው ከኾነ በተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው ነው የሚሉት፡፡ ትንንሽም ቢኾን መልካም ነገር የማናሳይ ከኾነ የተማሪዎች ዕይታ እየተበላሸ ነው የሚሄደው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ራሳቸውን እንዴት አድርገው ሰላም ማድረግ እንዳለባቸው ማስተማር ይገባል ነው ያሉት፡፡

የእነርሱ መኖር ለሀገር እና ለሕዝብ ጥቅም እንዳለው ማስተማር ይገባልም ብለዋል፡፡ ልጆች ትምህርት ቤት ባልሄዱ ቁጥር ማኅበራዊ ቀውስ እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡ ተማሪዎች ተስፋ ቢስ ነገር እየሰሙ በሄዱ ቁጥር ወደ አልተገባ ነገር ይገባሉ፡፡ ይህ ሲኾን ደግሞ ሀገር የሚያስፈልጋትን ትውልድ መፍጠር ያስቸግራል ነው ያሉት፡፡

ከትምህርት ውጭ የኾኑ ልጆች ከተማሩት ልጆች በአስተሳሰብ እና ዓለምን በመረዳት በኩል ፍጹም የተለያዩ ናቸው፤ ይሄም አስቸጋሪ ይኾናል ይላሉ፡፡ ጥናት አጥንቶ መፍትሔ ማበጀት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ሁልጊዜም ችግር ከኾነ የምናስበው እና የምንሰማው ሕይወትም የሚታጠረው በችግር ብቻ ነው፣ መልካም የኾኑ ነገሮችን፣ ሊያመጡ የሚችሉ ተስፋዎችን ማሳየት ይገባል ብለዋል፡፡

ወላጆች ስለሚያወሩት እና ስለሚያደርጉት ነገር ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ የትምህርት መሪዎች በግጭት ወቅት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች፣ ሽልማቶች እና ማበረታቻዎች ከወትሮው የተለየ መኾን አለበት ብለዋል፡፡ በቆዬው አካሄድ መሄድ ተማሪዎችን ሊያርቅ ይችላል ይላሉ መምህርቷ፡፡ ድሮ ተማሪ ሲቀር የሚያባርሩ፣ አሁን ማቅረብ፣ ትምህርት እና ትምህርት ቤትን እንዲወዱ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ የተመቻቸ ሥርዓት መፍጠር ተማሪዎች ትምህርቱን ወደውት እንዲመጡ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚያስችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።
Next articleተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የተላላፊ በሽታዎች ስርጭት እንዳይኖር እየተሠራ መኾኑን የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።