
ባሕር ዳር: መጋቢት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናስዮ ካሲስ በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ የሁሉቱ ሀገር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እንደተናገሩት በሁለቱ ሀገራት የጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ ውጤታማ ውይይት አድርገናል። የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መክረናል።
ሁለቱ ሀገራት የቆየ እና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አላቸው ያሉት አምባሳደሩ ከዳግማዊ ምኒልክ ጀምሮ ኢትዮጵያ ለማዘመን የስዊዘርላንድ ድጋፍ ጠንካራ መኾኑን ጠቅሰዋል። አሁንም ትብብሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
ስዊዘርላንድ ለኢትዮጵያ ትልቅ የገበያ መዳረሻ ናት ያሉት ሚኒስትሩ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እየተጠናከረ መምጣቱንም ገልጸዋል።
የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናስዮ ካሲስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ በሁለትዮሽ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጠንካራ ትብብር መኖሩን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ ጠንካራ የንግድ ግንኙነት አላቸው ያሉት አምባሳደሩ 20 የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ተሰማርተው እንደሚገኙ እና የኬሚካል እና የፋርማሲ ውጤቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላኩ ገልጸዋል። ስዊዘርላንድ ቡና እና ወቅርን ከኢትዮጵያ እንደምትወስድ በመግልጽ የንግድ ትብብሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል መባሉን ኢፕድ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
