
እንጅባራ: መጋቢት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ለ2016/17 የመኸር ሰብል ልማት 842 ሺህ 303 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመጠቀም ታቅዷል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ለምርት ዘመኑ ከታቀደው ግብዓት ውስጥ እስከ አሁን ድረስ 404 ሺህ 38 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ማዕከላዊ መጋዘኖች ደርሷል። ይህም ለምርት ዘመኑ ከሚያስፈልገው ግብዓት ውስጥ 48 በመቶ ነው ተብሏል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ አዲሱ ስማቸው የዘንድሮው የማዳበሪያ አቅርቦት ወቅቱን ጠብቆ በታቀደው ልክ እየቀረበ መኾኑን ተናግረዋል። እስከ አሁን ድረስ ወደ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ማዕከላዊ መጋዘኖች ከደረሰው 404 ሺህ 38 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 101ሺህ ኩንታል የሚጠጋው ወደ ወረዳዎች ተጓጉዞ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ እንደኾነም ምክትል ኀላፊው ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ያጋጠመው የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ከስርጭት ፍትሐዊነት መጓደል ጋር ተዳምሮ በሰብል ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን የገለጹት ምክትል ኀላፊው ችግሮች እንዳይደገሙ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በ2016/17 የምርት ዘመን ከ327 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የመኸር ሰብሎች እንደሚለማ ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!