የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በተገኘው ሰላም የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።

18

ደብረ ብርሃን: መጋቢት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በተገኘው ሰላም የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ባለፉት ሰባት ወራት 17 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መግባታቸውን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ 35 ፋብሪካዎችን ወደ ማምረት ለማስገባት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።

በከተማዋ የሚታየውን አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን ከ39 ሺህ በላይ ሰነዶችን በዲጂታል ሲስተም ማስገባት መቻሉንም አንስተዋል። ከ5 ሺህ 300 በላይ ለሚኾኑ ዜጎች ከሳምንት በኋላ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ለማስረከብ ዝግጅት ተደርጓል።

በከተማው የሚገኙ 82 ትምህርት ቤቶች በማስተማር ላይ ይገኛሉ ያሉት ተቀዳሚ ከንቲባው ሌሎች የልማት ሥራዎችም በሰላማዊ መንገድ እየተከናወኑ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ በታቀደው መንገድ እየተከናወነ አለመኾኑን ያነሱት ተቀዳሚ ከንቲባው በቀጣይ ወራት ለማሳካት ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ እየተከናወኑ በሚገኙ የልማት ሥራዎች ላይ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል። የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተቀመጠላቸው ጊዜ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ማኅበረሰቡ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለሀገር አቀፉ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በምናደርገው ዝግጅት የመጻሕፍት እጥረት ችግር ፈጥሮብናል” ተማሪዎች እና መምህራን
Next articleከ404 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ መግባቱን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።