“ለሀገር አቀፉ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በምናደርገው ዝግጅት የመጻሕፍት እጥረት ችግር ፈጥሮብናል” ተማሪዎች እና መምህራን

24

ደብረ ብርሃን: መጋቢት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና ተማሪዎች ለሀገር አቀፉ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በሚያደርጉት ዝግጅት የመጻሕፍት እጥረት ችግር እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

ተማሪዎቹ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በግላቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር የትምህርት ቤቱ መምህራን እና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህራን ድጋፍ እያደረጉላቸው እንደኾነ አንስተዋል።

ተማሪ ሕይዎት አየለ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪ ስትኾን መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት እየሠጧቸው እና ያለፉ ዓመታት የፈተና ጥያቄዎችን እየሠሩላቸው ስለመኾኑ ተናግራለች።
ይሁን እንጅ ከኢኮኖሚክስ፣ ከአይሲቲ እና ከእንግሊዝኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት ውጭ ሌሎች መጻሕፍት አለመኖራቸው፣ ያሉትም ሥርጭታቸው 1 ለ 4 በመኾኑ እየተቸገርን ነው ብላለች።

በተመሳሳይ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪው የአብሥራ ጌታቸው ሁሉም መጻሕፍት እንዳልተሰጣቸው እና ትምህርታቸውን በሶፍት ኮፒ ብቻ እየተከታተሉ መኾኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቱ የሥነ ሕይወት መምህር የኾኑት ጌታቸው ማሞ በበኩላቸው የመጻሕፍቱ በበቂ ሁኔታ አለመቅረብ በመማር ማስተማሩ እና በተማሪዎች ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አንስተዋል። መምህር ጌታቸው የፅንሰ ሀሳብ ትምህርትን በቤተ ሙከራ ለመደገፍም ኬሚካሎች የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው በመኾናቸው ችግር እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሳሙኤል አለማየሁ በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከመምህራን ባሻገር የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ እና የቀድሞ ተማሪዎች ኅብረት ለተማሪዎች ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል።

የመጻሕፍት አቅርቦት ችግር መኖሩን የገለጹት ምክትል ኀላፊው እጥረቱን ለመቅረፍ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በመነጋገር ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል። ሰሞኑን የሚሰራጩ ተጨማሪ መጻሕፍት መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል መምሪያ ኀላፊው አሁንም ችግሩን ሙሉ በሙሉ የሚፈታ የመጸሐፍ ቁጥር አለመቅረቡን ገልጸዋል።

የቀረቡትን መጻሕፍትም በሚፈለገው ፍጥነት ከክዘና ማዕከላት ወደየትምህርት ቤቶች ለማሰራጨት የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር እንዳለባቸውም አንስተዋል:: አቶ ሳሙኤል የመጻሕፍት እጥረቱ ሙሉ በሙሉ እስኪቀረፍ ተማሪዎች እና መምህራን ሶፍት ኮፒዎችን በመጠቀም የመማር ማስተማር ሂደቱን አጠናክረው ሊያስቀጥሉ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በትምህርት ዘመኑ በከተማ አሥተዳደሩ 2 ሺህ 358 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናን ይፈተናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የትምህርት መምሪያው መረጃ ያመለክታል።

ዘጋቢ:- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ላደረገው ያላሳለሰ ድጋፍ እናመሰግናለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር በተገኘው ሰላም የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።