በማኅበረሰቡ ተሳትፎ በ50 ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጭ አምስት መድኃኒት ቤቶች ተገንብተው መጠናቀቃቸውን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ገለጸ።

15

ደሴ: መጋቢት 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከእቅዱ ከ88 በመቶ በላይ የጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን መምሪያው ገልጿል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የጤና መምሪያ ኀላፊ ሰዒድ የሱፍ ለአሚኮ እንደገለጹት በመንግሥት ተቋማት በአቅም እና አሠራር ችግር ምክንያት በሚፈጠር የመድኃኒት እጥረት ታካሚዎች ለመድኃኒት ግዥ ከፍተኛ ወጭ ያወጣሉ።

በተለይ ደግሞ የጤና መድኅን ታካሚዎች የጤና መድኅን ደብተራቸውን ብቻ ይዘው ለሕክምና ወደ ጤና ተቋማት ስለሚጓዙ በሕክምና ጣቢያው የሌሉ መድኃኒቶችን ውጭ ላይ ለመግዛት እንደሚቸገሩ ነው የገለጹልን።

ተገልጋዮች ገንዘብ ኖሯቸው መግዛት ቢችሉ እንኳን መንግሥት ካስቀመጠው ተመን በላይ በኾነ ወጭ ስለሚገዙ የኪስ ትክ ገንዘቡ እንደማይመለስላቸው ነግረውናል።

ችግሩን ለመቅረፍ የማኅበረሰብ እና የመንግሥት ተቋማት መድኃኒት ቤት እዲከፍቱ መደረጉን አንስተዋል። ይሁን እንጅ የተከፈቱት መድኃኒት ቤቶች ከደሴ ከተማ ውጭ ለሚገኘው ማኅበረሰብ ጭምር አገልግሎት ስለሚሰጡ ችግሩን መቅረፍ አለመቻሉን አንስተዋል።

መምሪያ ኀላፊው እንዳሉት የሚታየውን የመድኃኒት እጥረት ለመቅረፍ በማኅበረሰቡ ተሳትፎ 50 ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጭ አምስት መድኃኒት ቤቶች ተገንብተው ተጠናቅቀዋል።
መድኃኒት ቤቶችን ለማሥተዳደር ከተማ አሥተዳደሩ ደንብ እያዘጋጀ እንደሚገኝ የገለጹት ኀላፊው ከአንድ ወር በኋላ ሙሉ በሙሉ ሥራ ይጀምራሉ። ሥራውን ለማስጀመርም ከተማ አሥተዳደሩ 25 ሚሊዮን ብር መድቧል ብለዋል።

መድኃኒት ቤቶች ለተገልጋዮች በችርቻሮ ከማቅረብ ባለፈ በጅምላ ለመንግሥት ተቋማት መድኃኒት ማቅረብ እንዲችሉ እየተሠራ ይገኛል ተብሏል። ከጤና መድኅን ተጠቃሚዎች ባለፈ ለሌላው ማኅበረሰብም አገልግሎት የሚሰጡ ይኾናል።

በደሴ ከተማ አሥተዳደር የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ ከታቀደው 46 ሺህ 666 አባወራ ውስጥ 88 ነጥብ 5 በመቶ አባል ማድረግ ተችሏል። በቤተሰብ ደረጃ ደግሞ 200 ሺህ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመቋጫው የራቀው የመገጭ ግድብ
Next article“የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ላደረገው ያላሳለሰ ድጋፍ እናመሰግናለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)