
ባሕር ዳር: መጋቢት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመገጭ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ ብሎም በክልሉ በርካታ ለውጦች ታይተዋል። ፕሮጀክቶች ተጀምረው ተፈጽመዋል። መሪዎች ሄደው መሪዎች መጥተዋል። በመገጭ ሰማይ ሥር ግን ከቀናት መንጎድ እና ከዓመታት መደራረብ የዘለለ የታየ ለውጥ የለም።
“ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ” ይሉት ቢሂል ደርሶበታል። ውኃ የሚጠማቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ለዓመታት የውኃ መቅጃቸውን አጉድለው ጠብቀውታል። ከዛሬ ነገ መገጭ ተጠናቅቆ እንስራዎች ይሞላሉ፣ የውኃ ማስተላለፊያዎች ውኃን ይይዛሉ እያሉ ለዓመታት ጠበቁ። የተባለው ተስፋ ግን በተባለው ጊዜ አልመጣም።
የጎንደር ከተማ ነዋሪው ሠርጸማርያም ያለው የመገጭ ግድብ ሲጀመር ታላቅ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር ያስታውሳሉ። በአምስት ዓመታት የሥራ ጊዜ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ይኾናል ተብሎ ነበር። መገጭ ግን እንኳን በታቀዱለት ዓመታት ይቅርና በሁለት እጥፍም አልተጠናቀቀም።
የመገጭ ግድብ ከግድቡ በታች የሚገኙ አካባቢዎችን በስፋት ያለማል ተብሎ ታስቦ እንደነበር ነው የሚገልጹት። ሥራው ከተጀመረ በኋላ የግድቡ 30 በመቶ ለጎንደር ከተማ የንፁህ ውኃ መጠጥ አገልግሎት ይውላል መባሉንም ነግረውናል። ለዓመታት ሲሠራ እናያለን ነገር ግን አይጠናቀቅም፤ ሁልጊዜም ባለበት የሚረግጥ ፕሮጀክት ነው ይላሉ።
መገጭ በአጀማመር ከዓባይ ግድብ ይቀድማል፤ ነገር ግን ባለበት የቆመ ግድብ ነውና ለውጥ አይታይበትም። የከተማዋ ነዋሪዎች በአስቸኳይ እንዲጠናቀቁላቸው የሚፈልጓቸው ፕሮጀክቶች አለመጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል። መገጭ ስለ ምንድን ነው? የማይጠናቀቀው የሚለው የሚመለከተው አካል ተጠይቆ እልባት መሰጠት አለበትም ይላሉ።
መገጭ ለዓመታት አፈሩ እየተቆፈረ፤ ወንዙ እየወሰደው ጣናን በደለል እየሞላ ነውም ይላሉ። መገጭ ካልተጠናቀቀ ተፈጥሮ የሰጠን ጣና በደለል ይሞላል ነው የሚሉት። የከተማዋ ነዋሪዎች ተስፋ ያደረጉበት ግድብ እንዲሁ በተስፋ ብቻ ቀጥሏል። ከተማዋ በውኃ ችግር ላይ ናት። በከተማዋ እንደ አካባቢው በሳምንት፣ በ10 ቀናት፣ በ15 ቀናት ውኃ እንደሚመጣም ነግረውናል። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ እስከ ወር ድረስ የሚቸገሩ እንዳሉ የሚናገሩ አሉም ይላሉ።
ከደንቢያ ይመጣል የተባለው ውኃም በታሰበው ልክ ሳይኾን መቅረቱን ነው የገለጹት። የጎንደር ከተማ የውኃ ችግር ሰፊ እና ጥልቅ መኾኑንም ነግረውናል። በንጉሡ እና በደርግ ዘመን ለከተማዋ ንፁህ የመጠጥ ውኃ የተቆፈሩ ጉድጓዶች መጥፋታቸውንም ገልጸዋል። የእነዚህ ጉድጓዶች መጥፋት ደግሞ ተለዋጭ ላልተሠራለት ከተማ የውኃ ችግሩን አባብሶታል።
ጎንደር ከተማ በተፈጥሮ የውኃ ማማ ነው፤ ያለውን የከርሰ ምድር ውኃ መጠቀም የከተማውን የውኃ ችግር ይቀርፋል ነው ያሉት። ቁጭ ብሎ በመነጋገር ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ መሥራት ይገባል ብለዋል። ጎንደርን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ የውኃ አማራጮች አሉ የሚሉት አቶ ሠርጸማርያም የጎንደር ከተማን የመሠረቱ አባቶች ወንዞችን ታሳቢ አድርገው የመሠረቷት ከተማ መኾኗን ነው የተናገሩት።
ከተማዋ በውስጧ እና በዙሪያዋ የሚገኙ ወንዞችን በአግባቡ ማልማት ቢቻል የውኃ ችግሩን መፍታት ይቻል ነበር ነው ያሉት። የከተማዋን የውኃ ችግር መፍታት ካስፈለገ ቁጭ ብሎ በመምከር ወደ ሥራ መግባት ይገባል ብለዋል።
የመገጭ ግድብ ግንባታ ተጠሪ መሐንዲስ ኢንጂነር ወርቅነህ አሰፋ የመገጭ ግድብ ችግሮች የተጋረጡበት ኾኖ መቆየቱን ገልጸዋል። የነበረውን ችግር የሚቀርፍ ጥናት በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል። ሥራውን በተባለለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ባለበት ጊዜ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ሁኔታ፣ የተቋራጩ ችግር እና አሁን ደግሞ የነዳጅ እጥረት ከእቅዱ በጣም አዘግይቶታል ነው ያሉት።
ተቋራጩ በቂ ማሽነሪዎችን አለማስገባት ለሥራው እንቅፋት ኾኖ መቆየቱንም አንስተዋል። በ2016 ይሠራል ተብሎ ከተያዘው እቅድ በእጅጉ ዘግይቷልም ብለዋል። በ2016 የተያዘውን እቅድ ማሳካት ባይቻልም የተሻለ ሥራ ለመሥራት ጥሩ እንቅስቃሴ ተጀምሮ በነበረበት ጊዜ የነዳጅ ችግር ፈተና ኾኗል ነው ያሉት። የነዳጅ ችግሩን ለመፍታት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ማገዙን ያነሱት ኢንጂነሩ የነዳጅ አቅርቦቱ ችግር ግን ከዚያም ያለፈ አማራጭ ያስፈልገዋል ብለዋል።
የጸጥታ ሁኔታው የነዳጅ አቅርቦት በተፈለገው ልክ እንዳይኾን ማድረጉንም አንስተዋል። የነዳጅ እጥረቱ ማሽነሪዎች እንዲቆሙ ማድረጉንም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ታላቅ እገዛ እንዲያደርግ ይጠበቃልም ብለዋል።
ተቋራጩ ችግሮችን እየተጋፈጠ መሥራት እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል። ከአቅሙ በላይ ሲኾን ደግሞ ድጋፍ እንዲደረግለት መጠየቅ አለበት ነው ያሉት። የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር በመኖሩም አጥጋቢ ሥራ አለመሠራቱን ገልጸዋል።
መገጭ 65 ነጥብ 8 በመቶ አጠቃላይ የግድቡ ሂደት መድረሱንም አንስተዋል። በርካታ ሥራ ይሠራበታል ተብሎ በታሰበበት በ2016 ዓ.ም እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አለመሠራቱን ነው የተናገሩት። የመገጭ ግድብ ለመስኖ ልማት፣ ለጎንደር ከተማ የንፁህ መጠጥ ውኃ እና ለዓሳ ሃብት ጥቅም ይውላል ተብሎ ነው ተስፋ የተጣለበት። የመገጭ ግድብ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሥራ መኾኑንም አመላክተዋል። በተለይም ተቋራጩ በቂ ሥራ እየሠራ አለመኾኑንም ተናግረዋል።
ተቋራጩን በሚገባ መከታተል እና ሥራውን በአግባቡ እንዲሠራ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። መንግሥት እጁን አስገብቶ ማገዝ እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል። መንግሥት ልዩ ትኩረት በማድረግ ማን ምን አጉድሏል የሚለውን በመለየት እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) ባለፈው ወር በተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ስለ መገጭ ግድብ ሲናገሩ የመገጭ ግድብ ቢሯቸው አጥንቶ ወደ ሥራ የገባበት ፕሮጀክት እንደነበር አስታውሰዋል። ፕሮጀክቱ በ2005 ዓ.ም በ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል። በ2012 ዓ.ም ደግሞ በአግባቡ እንዲሠራ ለማድረግ መሻሻሉንም አስታውሰዋል። እቅዱ ሲሻሻል የሚገነባበት የገንዘብ መጠንም 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል።
መገጭ 185 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የመያዝ አቅም እንዳለው ያነሱት ኀላፊው 33 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚኾነው ደግሞ ለጎንደር ከተማ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት የሚውል መኾኑንም አንስተዋል። በ2012 ዓ.ም ተሻሽሎ የቀረበው በሰከንድ 900 ሊትር የሚያመነጭ መኾኑንም ተናግረዋል። የመገጭ ግድብ በታሰበው ልክ አለመሄዱንም ገልጸዋል። የመገጭ ግድብ ችግር ያለው ከተቋራጩ መኾኑንም አመላክተዋል።
ፕሮጀክቱ ልምድ ላላቸው ድርጅቶች ተሰጥቶ መሥራት ካልተቻለ አስቸጋሪ መኾኑንም ገልጸዋል። የመገጭ ግድብን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ እንደማይቻልም አንስተዋል። መሪዎች በጎበኙት ቁጥር ተቋራጩ በዚህ ቀን ይጠናቀቃል በማለት የሕልም እንጀራ ኾኗል ነው ያሉት። ጎንደር ላይ ትልቁ ችግር ውኃ ነው ያሉት ኀላፊው የውኃ ችግሩን መፍታት ከተቻለ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ያሳድጋል፣ የከተማዋ ልማት እና እድገትም ከፍ ይላል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን በልዩ ሁኔታ እንዲሠራ የማድረግ ኀላፊነት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል። የውኃ ጉዳይ ለነገ የሚባል አለመኾኑንም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የመገጭ ግድብ በመጥፎ ፕሮጀክት አመራር የሚገለጥ መኾኑን ተናግረዋል። በሚቀጥሉት ወራት የመገጭ እድል መታወቅ አለበትም ነው ያሉት።
ለፕሮጀክቱ በየጊዜው የሚቀያየር በርካታ ምክንያት እንደሚቀመጥ ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ወደፊት ቁርጥ ያለ ነገር ማቅረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የመንግሥት የመፈጸም ድክመት ማሳያ እየኾነ መቀጠል የለበትም ብለዋል። ፕሮጀክቶችን በየጊዜው መከታተል እና በአግባቡ መምራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!