ከገቡበት ድባቴ እየነቁ የሚገኙ ሀገራት

46

ባሕርዳር: መጋቢት 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንዱ የሌላውን በመውሰድ በጋራ ማደግ፣ እርስ በእርስ መጠቃቀም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጎላ የመጣ በጋራ የማደግ እና የመበልጸግ ርዕይ ነው፡፡ ይህ እሳቤ ቢዘገይም አኹን ላይ ለመተግባር መንቀሳቀስ መጀመሩ ግን አሰየሁ የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡

የጋራ መድረክ መፍጠር ላይ ኢትዮጵያ የምትታማ ሀገር አይደለችም፡፡ ተሞክሯዋም ሰፊ ነው፡፡ በርካታ ሊጠቀሱ የሚችሉ ተግባራቶችም አሏት፡፡ ኢትዮጵያ የመሰረተቻቸው የጋራ ጉባኤዎች ከአፍሪካ ኅብረት እስከ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ድረስ ውጤታማ ሥራዎችን ሥትሠራም ቆይታለች፡፡

አፍሪካውያን በቅኝ ዘመን ጊዜም አለመተባበራቸው እና አብሮ አለመሥራታቸው ለቅኝ ግዛት ዳርጓቸዋል፡፡ የኋላ ኋላ ግን መተባበር ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት መተባበር ሲጀምሩ ሁሉም ከቅኝ አገዛዝ እንዲወጡ አስችሏቸዋል፡፡ አፍሪካውያን አኹንም ቢኾን ከቅኝ ግዛት ቢወጡም አንቆ የያዛቸው ድህነት ከኢኮኖሚ የቅኝ ግዛት እንዲወጡ አላስቻላቸውም፡፡

ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በሚባል ደረጃ በግብዓት በኩል ሰፊ የጥሬ እቃ ያለባቸው ቢኾንም፣ የሃብት ማማ ላይ መውጣት የሚያስችል ሃብት በጉያቸው አቅፈው ቢይዙም አኹንም ድረስ ያላቸውን ሃብት አውጥተው መጠቀም ግን አልቻሉም፡፡

አንዱ የአፍሪካ ሀገር ያለውን ለሌለው በንግድ ትስስር መፍጠር እና መቀየር እየቻሉ ግን ይህን ማድረግ ለረዥም ጊዜ ተስኗቸው ቆይቷል፡፡ አፍሪካውያን ሀብታቸውን በሌሎች የበለጸጉ ሀገራት እየተነጠቁ የበይ ተመልካች ከመኾን አሁንም አልተሻገሩም፡፡

አፍሪካውያን አኹን ላይ ከነበረባቸው ድባቴ በመጠኑም ቢኾን የነቁ የሚመስሉ እርምጃዎችን ሲወስዱም እየተስተዋሉ ነው፡፡ የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጠውን የነፃ ንግድ ቀጣና ለመተግበር ጥረቶች ሲደረጉም እየተስተዋለ ነው፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የኢኮኖሚ ልማት፣ የንግድ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽነር አምባሳደር አልበርት ሙቻንጋ እንደሚሉት የአፍሪካውያንን የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጠውን የነፃ ንግድ ቀጣና ለመተግበር የሚደረጉ ጥረቶች አኹንም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ባይ ናቸው፡፡

ነፃ የንግድ ቀጣና ከካይሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ፤ ከሞሪሺየስ እስከ ኬፕቨርዲ ያለውን ሰፊ ገበያ የሚመለከትና ሚሊዮን አፍሪካውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት ስለመኾኑም ነው በአጽንኦት የሚገልጹት።

ይህ ዘርፍ ለአፍሪካውያን በርካታ እድሎችን ይዞ ሊመጣ የሚችል እንደኾነም ነው ያስረዱት፡፡ አፍሪካውያንን በ1 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር ራዲየስ ማስተሳሰር ለጋራ ልማትና ብልጽግና አስፈላጊ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ይህን ተግባር ውጤታማ ለማድረግ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ትኩረት የሰጠች ሲኾን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል አፍሪካን በትራንስፖርት ለማስተሳሰር የተሠራው ሥራ ውጤታማ በመኾኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል፡፡

አፍሪካን ለመቀየር ትልቁ መሳሪያ ነፃ የንግድ ቀጣና በመኾኑ የሀገራቱን የንግድ ልውውጥ ከማሳለጥ ባሻገር የውስጥ የምርት አቅምን ለማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን ለማጎልበት እና ለሥራ ፈጠራ ነፃ የንግድ ቀጣናው ኹነኛ አቅም ይኾናልም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የክልሉ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስገነዘቡ።
Next articleበኩር ጋዜጣ መጋቢት 09/2016 ዓ.ም ዕትም