በአማራ ክልል የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የክልሉ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስገነዘቡ።

29

አዲስ አበባ: መጋቢት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ክልል ተወካዮች ከርእሰ መሥተዳደሩ ጋር ባደረጉት ውይይት የሕዝብ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ለጥያቄዎቹ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ርእሰ መሥተዳድሩ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝቡ ላልተፈለገ ችግር መጋለጡን ገልጸዋል።

ከዓለም እና ሀገር አቀፍ እውነታ ጋር በተያያዘ ያጋጠመው የግንባታ ቁሳቁስ መናር በክልሉ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዳይጠናቀቁ ምክንያት ኾነዋል ነው ያሉት። ይህ ደግሞ በቀላል ወጭ መጠናቀቅ የሚችሉ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ባለመጠናቀቃቸው ክልሉን ለከፍተኛ ወጭ እንደዳረገውም ገልጸዋል።

ከትምህርት ጋር በተያያዘ በክልሉ ከ3 ሺህ 700 በላይ ትምህርት ቤቶች በሰላም እጦት ምክንያት ሥራ አለመጀመራቸውን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ በዚህም ከ3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም እንደ ሕዝብ የተነሱ እና ለኑሮ ውድነት መፈጠር ምክንያት የኾኑ ጉዳዮች አሉ ብለዋል። ይህን ለመከላከልም ሕግ የማስከበር ሥራችንን በማጠናከራችን ቀላል የማይባል ለውጥ አምጥተናል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ።

በተለይም ሕገወጥ ንግድን መከላከል እና የሸማች ማኅበራትን እና ዩኒየኖችን በማቀናጀት መሥራት ለነገ የማይባል የቤት ሥራ መኾኑን አንስተዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ ከመዋዕለ ንዋይ ፍሰት፣ ከጤና እና ከመሰረተ ልማት አንጻር ክልሉ ያለበትን ሁኔታ ለሕዝብ ተወካዮች አባላት አስረድተዋል።

እነዚህን እና ሌሎች የክልሉ ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመለሱ ደግሞ የክልሉ የጸጥታ ችግር መቀረፍ አለበት ብለዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ ለዚህም የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ ኾኖ እየሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማኅበረሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።
Next articleከገቡበት ድባቴ እየነቁ የሚገኙ ሀገራት