
ደብረ ብርሃን: መጋቢት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር መንገድ መምሪያ በከተማ አሥተዳደሩ ውስጥ የሚገኘውን የመሬት ይዞታ ጥራት ባለው የመረጃ ሥርዓት በምዝገባ ሂደት እንዲያልፍ እየሠራ መኾኑን ገልጿል።
የመምሪያው ኀላፊ እታለማው ይምታቱ የመሬት ይዞታ ምዝገባው ዓላማ በዋናነት ሀብቱን ለመለየት፣ ይዞታው በማን፣ መቼ፣ ለምን አገልግሎት እና በምን ሁኔታ ጥቅም ላይ እንደሚውል ግልጽ አሠራር ለመዘርጋት ነው ብለዋል።
በከተማው የሚገኙ ባለይዞታዎች በመሬታቸው ላይ ያፈሩትን ሀብት በዋስትና በማስያዝ በከተማው ውስጥ ከሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መጠቀም የሚችሉበት እድል ለማመቻቸት ይሠራል ነው ያሉት።
ዘመናዊ የመሬት መረጃ ሥርዓቱ የይዞታውን ዘለቄታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ የአገልግሎት አይነትን ለመለየት፣ በይዞታው ላይ ያለን የማይንቀሳቀስ ንብረት ልውውጥ ተቀባይነት ባለው የሕግ ማስረጃ እንዲደገፍ ለማድረግም እንደሚያግዝ ተገልጿል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ ተግባሩ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እኩል ትኩረት ተሰጥቶት መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።
ከይዞታ ይገባኛል እና የወሰን ይከበርልኝ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ሕጋዊ እና ተአማኒ የመሬት ምዝገባ ሥርዓትን መገንባት ወሳኝ ተግባር መኾኑንም አስረድተዋል።
ዛሬ ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝ ሥርዓትን ለማጠናከር እና በሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮችን ለማቃለል ያለመ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።
ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!