ነዳጅን እንደ ማስቲካ…..

70

ባሕር ዳር: መጋቢት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሦስተኛው ሚሊኒየም መግቢያ 2000 ዓ.ም ሲጀመር የሸቀጦች ዋጋ መናር እና የኑሮ ውድነት ተከስቶ ነበር።

ነጋዴዎች የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶችን በመደበቅ ሰው ሰራሽ እጥረት ፈጠሩ። በቀጣይም ምርት እና ሸቀጥ እንደሚጠፋ አስወሩ። ሕዝቡም ‘ክፉ ቀን መጣ’ ብሎ በመሸበር ገንዘቡን አሟጥጦ ወደ ሱቆች እና ገበያ በመጉረፍ ሸቀጦችን ለመሸመት ተሻማ።

ማኅበራዊ ኀላፊነት የማይሰማቸው ነጋዴዎችም ሸቀጣቸውን በፈለጉት ዋጋ ሸጡ። እሱን ተከትሎም መንግሥትም ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ መሠረታዊ ሸቀጦችን በማቅረብ፣ ዋጋ በመወሰን እና ቁጥጥር በማድረግ የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ ጥረት ማድረጉን አስታውሳለሁ።

ከዚያ ወዲህም በዓለም አቀፍም ኾነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ መናር፣ የኑሮ ውድነት እና ተያያዥ ችግሮች ተፈጥረው ያውቃሉ። የምርት እጥረት እንዳለ፣ አምራቾች ዋጋ እንደጨመሩ፣ ክፉ ጊዜ እንደመጣ፣ ወዘተ በማስወራት ያልተገባ ሃብት ለማግኘት የሚሞክሩ አምራቾች፣ ነጋዴዎች እና ደላሎችንም አስተውለናል።

የነጋዴዎች እና የደላላዎች ስግብግብነት ብቻ ሳይኾን ከበርቴዎችም ገንዘብ ስላላቸው ብቻ ሸቀጡን ሁሉ ጠቅልለው በመግዛት ለዝቅተኛው ነዋሪ እና ለድሃ አዳሪው አላተርፍ ሲሉ አይተናል። የተጠየቁትን ዋጋ በመክፈልም ለሸቀጦች ዋጋ መናር ሲተባበሩ እና በድሃው ጉሮሮ ላይ ሲቆሙ አስተውለናል።

በአማራ ክልል በኮሮና ወረርሽኝ እና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በሥራ እጦት፣ በሸቀጦች ዋጋ መናር እና በኑሮ ውድነት ሲንገላታ የቆየው ሕዝብ አሁን ደግሞ በተከሰተው ግጭት ምክንያት የምርቶች እና አገልግሎቶች ዋጋ በመናሩ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው።

ድሮ ድሮ ምን ችግር ቢፈጠር በምርት እና አገልግሎታቸው ላይ ዋጋ የማይጨምሩት፤ ከጨመሩም በምክንያት፣ በፍትሃዊነት እና አሳውቀው የነበሩት ታላላቅ ተቋማት ዛሬ ግን በሕዝቡ ላይ የፈለጉትን ያህል ዋጋ ይጨምሩበት ይዘዋል። አንዱ ችግር ከሌላው እየተመጋገበ የተደራረበው ችግር እናት ለልጇ ዳቦ መግዛት የሰማይ ያክል እንዲርቃት አድርጓታል። መቶ ግራም መሙላቱ ያልተረጋገጠ ዳቦ ዋጋም 10 ብር ደርሷል።

በተፈጠረው የሰላም እጦት ሕዝቡን አንገቱን አንቀው ካስመረሩት ችግርች መካከል የነዳጅ በሕገ ወጥ መንገድ መቸብቸብ አንዱ ነው። ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ ኾነና በተፈጠረው የፀጥታ እና የደኅንነት ችግር ምክንያት እንደልብ ተንቀሳቅሶ መሥራት ያልቻለው ሕዝብ አሁን ደግሞ በሕገ ወጥ የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ምክንያት በከፋ ኑሮ ውድነት እያለፈ ይገኛል። ነዳጅ ሲጠፋ ዘይትም ዋጋው ሲጨምር በርካታ ሸቀጦች እና አገልግሎታቸው መናር ደግሞ የተለመደ ኾኗል።

ከነዳጅ ጋር በተያያዘ የገጠመን ችግር የዘንድሮው የተለየ ነው። ለወትሮው ነዳጅ ሲጠፋ ወይም ዋጋው ሲጨምር የሚፈጠረውን የኑሮ ውድነት ተጽዕኖውን ለመቀነስ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ትኩረት ሰጥተው ክትትል እና ቁጥጥር ያደርጉ ነበር። ሕዝቡም ቢኾን ለሕገ ወጥነት ባለመተባበርም ኾነ ጫና በማሳደር የመፍትሔው አካል በመኾን ጉልህ ሚና ነበረው።

ነጋዴዎችም ጫጫታው እና ምሬቱ ጠንከር ሲል የደበቁትን ምርት የማውጣት የሰቀሉትን ዋጋ የማውረድ ባሕሪ ነበራቸው። ዛሬ ግን ለክልሉ የሚቀርበው ነዳጅ እጥረት ሳይኖር ዋጋ ሳይጨምር ማደያዎች ነዳጅ በአግባቡ ባለማከፋፈላቸው የኑሮ ውድነቱ ተባብሷል። በግጭቱ ምክንያት ሥርዓት አልበኝነት መኖሩ፣ መንግሥት በዚህ ሥራ መጠመዱ እና የሕዝቡ ተስፋ መቁረጥ የተገነዘቡ የነዳጅ ማደያዎች የድሃውን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ ማድረጉን ቀጥለውበታል።

በሀገር ደረጃ እንደ አዲስ የጨመረ የነዳጅ ዋጋ የለም። መጠኑ እየቀነሰ ቢሄድም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሃብቶች የነዳጅ ዋጋ ድጎማ ይደረጋል። አማራ ክልልም በፀጥታ ችግር ውስጥ ኾኖ እንኳ ነዳጅ መግባቱ አልቀረም። ይሁንና የትራንስፖርት ባለሃብቶች የተደረገላቸውን ድጎማ ታሳቢ ያደረገ ፍትሃዊ ዋጋ ከማስከፈል ይልቅ ወቅታዊ ችግሩን ሽፋን በማድረግ ከሕጋዊ ዋጋው (እስከ አምስት) እጥፍ የማስከፈል ጭካኔ ተላብሰዋል። ሕዝቡም ”ለማን አቤት ይባላል? እሱ ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው መቻል ነው እንጂ” በሚል ተስፋ መቁረጥ ስሜት የተጠየቀውን ይከፍላል።

በማኅበራዊ እና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ዘርፍ ተሰማርቶ ሕይወቱን መምራት የሚፈልግ ሰው በነዳጅ ውድነት ምክንያት ከኮሮና ወረርሽኝ ጊዜ በባሰ የእንቅስቃሴ ገደብ ተፈጥሮበታል። ለወትሮው በመንግሥት የሚወጣው የነዳጅ ዋጋ ተመን ቶሎ ቶሎ የማይቀየር፤ ቢቀየርም ቅናሽ ወይ ጭማሪው በሳንቲሞች ደረጃ የተወሰነ ነበር። የዘንድሮውን ልዩ የሚያደርገው የዋጋው መናር ብቻ ሳይኾን ነዳጅ ከማደያ ወጥቶ በየቦታው መቸብቸቡ ጭምር ነው።

በዓለም የነዳጅ ዋጋ፣ በዶላር የምንዛሪ መጠን መጨመርም ወይም በትራንስፖርት ችግር የማይመካኝበት የዘንድሮውን የአማራ ክልል ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ በየደረጃው ያሉ የንግድ እና ገበያ ልማት፣ የሕግ እና ደንብ ማስከበር፣ የፍትሕ እና የፀረ ሙስና አካላት በዝምታ ማለፋቸውም የሚገርም ነው።

የነዳጅ ማደያዎች ላይ አለቀ የተባለው ነዳጅ ሕገ ወጥ ነጋዴው ላይ በገፍ ይገኛል። መኪናዎች ነዳጅ ለመቅዳት ሥራ አቁመው በኪሎ ሜትሮች በሚለካ ርዝመት ተሰልፈው ውለው ካደሩ በኋላ አለቀ ይባላሉ። በጉልበተኝነት የተቧደኑ ”ጉልበተኛ” ግን ከሰዎች ገንዘብ ተቀብለው ለፈለጉት ባለመኪና ያለወረፋው ነዳጅ እንዲቀዳለት ያደርጋሉ፣ ነዳጅ ቀጂዎች በበኩላቸው እስከ 300 ብር ጉርሻ ተቀብለው ነዳጅ በጀሪካን ይሸጣሉ። ይህ በየቀኑ በየነዳጅ ማደያው ይስተዋላል። በጀሪካን እየተቀዳ የሚሸጠው ነዳጅ በሁለት ሊትር የውኃ መያዣ እየተሞላ እንደ ማስቲካ እና ሶፍት በአዟሪዎች ይሸጣል። እንደ ሳምንታዊ ፍጆታ ነዳጅ በግለሰቦች እጅ ተይዞ መታየትም ተለምዷል። ለምን ብሎ የሚጠይቅ ግን የለም። ”ማን ሊሰማ እና ሕግ ሊያስከብር? ለምንስ እጣላለሁ?” ኾኗል የሰው ተስፋ መቁረጥ።

ነዳጅ ማደያዎች ያለ እፍረት እና ፍርሃት በእጅ መንሻ ነዳጅ ሲቀዱ፤ ለማይመለከታቸው አካላት በጀሪካን ሲሸጡ፤ ተሰልፎ ተራውን የሚጠብቅ እያለ በጉልበተኞች ትዕዛዝ ወረፋ ላልጠበቁ መኪኖች ነዳጅ ሲቀዳ፤ ነዳጅ ቀጂዎች ጉርሻ ካልተሰጣቸው ሰበብ በመፍጠር አላስተናግድ ሲሉ፤ ይባሱኑ ነዳጅ ከማደያዎች ውጪ (በጥቁር ገበያ) በብዙ እጥፍ ዋጋ በየቦታው ሲቸረቸር እና እንደ ማስቲካ ሱቅ በደረቴዎች ይዘውት ሲዞሩ መታየት ከጀመረ ሳምንታት ተቆጠሩ።
አንድ ቀን መንገድ ዳር ተቀምጠን ቡና እንጠጣለን፤ አንድ ወጣት ልጅ በአምስት ባለ ሁለት ሊትር የውኃ መያዣ ላስቲክ ”ቤንዚን” ታቅፎ ሲሄድ አየነው።

ከመካከላችን አንዱ ”ይሸጣል?” አለው።
”አይሸጥም፤ ከፈለክ ግን አመጣልሃለሁ” ልጁ መለሰ
”እንዴት ላግኝህ?”
”ስልኬን ያዝ፤ 09……..” ስልኩን ሰጠ።

ከነዳጅ አዟሪው ጋር በተደረገ የመተማመን ውይይት ”እንደምንም ተፍ ተፍ …” ብለው ነዳጁን እንደሚያገኙት እና ለነሱም ”የሻይ እንዲያገኙ አድርገው” ዋጋ ተምነው እንደሚሸጡ አወራው።

ከማደያ የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ 77. 70 ብር ቢኾንም ”በጥቁር ገበያ” ግን አንድ ሊትር ከ200 እስከ 300 ብር እየተቸበቸበ ነው። ናፍታ ትክክለኛ ተመኑ በሊትር 79.80 ብር ሲኾን በጥቁር ገበያ ግን እስከ 100 ብር እየተሸጠ ነው። ማደያ ላይ አለቀ የተባለው ነዳጅ ያለ ቦታው ሞልቷል – ግን በውድ ዋጋ። ያለ ስጋት የሚታወቁ መሸጫ ቦታዎች ተለይተውለት ይሸጣል። ሰውም ሕገ ወጡን የነዳጅ ግዢ ተላምዶታል።

በዞን እና በወረዳ ከተሞችም ከማደያዎች አለቀ የተባለው ቤንዚን በጎሚስታ፣ በመኪና ማሳደሪያ እና ማጠቢያ ቦታዎች ተፈልጎ እንደማይጠፋ ለነዳጅ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ነግረውኛል። አንድን የከተማ ነዋሪ ቤንዚን የት አገኛለሁ ቢሉት ያለ ስጋት ቦታ ይጠቁምዎታል፤ ወይ ስልክ ቁጥር ሰጥቶ በዚህ ደውለህ ጠይቅ ይልዎታል።

በዚህ ሁሉ የነዳጅ ሕገ ወጥ ዝውውር እና ግብይት አድራሻቸው በከተሞች ብቻ የተወሰኑትን የነዳጅ ማደያዎች ሕግ አክብረው እንዲሠሩ እና ለኑሮ ውድነት መባባሱ ተጨማሪ ምክንያት እንዳይኾኑ መቆጣጠር ያለበት አካልስ ምን እየሠራ ይኾን? በፀጥታው መደፍረስ ምክንያት መሥራት አልቻልኩም ይላል? ወይስ የተፈጠረ ችግር የለም! ብሎ ያስደምመናል?

በኢትዮጵያም ኾነ በዓለም የኑሮ ውድነት ከሚከሠትባቸው ምክንያቶች ውስጥ የነዳጅ ዋጋ መጨመር እንደኾነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ። ከዚህ ቀደም የምናስታውሳቸው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪዎች በሰላም ጊዜ ይኾኑ እና በመንግሥትም በሕዝቡም ርብርብ ይደረግባቸዋል። እሱን ተከትሎ የሚመጣ የሸቀጦች ዋጋ መናርን ለመቆጣጠር ሲቻልም አይተናል። የጎላ ችግር ሳያደርስ ችግሩ ይታለፍም ነበር። የዘንድሮውን የከፋ የሚያደርገው አስቀድሞ የኑሮ ውድነቱ እና በዚያ ላይ ደግሞ የነዳጅ ሕገ ወጥ ሽያጭ መጨመሩ ነው። በትራንስፖርት ላይ የሳንቲም መልስ ይቀበል የነበረው ከተሜ እንኳ ለ5 ብሩ የታክሲ ዋጋ 10 ብር መክፈሉን ለምዶታል። ሕዝቡም 240 ብር ያስከፍል የነበረው 173 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ ከ300 እስከ 350 ብር በመክፈል የዋጋ መናርን አምኖ ተቀብሎ ያደረ ይመስላል። መከራከር የለ፤ ለሕግ አካላት ማመልከት የለ፤ በቃ! ችግሩን ተቀብሎ እና ቅሬታውን ባገኘው አጋጣሚ መግለጽ ብቻ በቂ ኾኗል።

መንግሥት ካወጣለት ተመን በላይ ሳንቲሞች ጨምሮ ቢሸጥ እንደ ሀገር ክዳት ተቆጥሮ ተጠያቂነት ይጠብቀው የነበረ የነዳጅ ማደያ ባለቤት ዛሬ ላይ ሲፈልግ ብቻ ማደያውን ከፍቶ ነዳጅ በውድ ዋጋ ይሸጣል። ካልፈለገ ደግሞ አልቋል ብሎ ዘግቶ በጨለማ በፈለገው ዋጋ ሲቸበችበው ያድራል። ለነዳጅ ቀጂዎች በሚሰጥ ”ጉርሻ” ስም ዋጋ ጨምሮ ሲሸጥ ‘ተመለስ’ የሚል ጠፍቷል።

ባሕር ዳርን ጨምሮ በአማራ ክልል ከተሞች የነዳጅ ሕገ ወጥ ሽያጭ እና ሥርጭት ከሌሎች ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ክስተቶች ጋር ተደማምሮ ሕዝቡን ለችግር ማጋለጡን ቀጥሏል። በሂደት እየተሸረሸረ የመጣው በመተዛዘን እና በመረዳዳት ክፉ ቀንን የማለፍ ባሕልም ዛሬ ዛሬ ‘አንድ ሐሙስ የቀረው’ መስሏል። የአምራቾች፣ አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎች ምርት መደበቅ ብቻ ሳይኾን አንዳንድ ሸማቾችም ከሚያስፈልጋቸው በላይ በመሸመት ብሎም ገንዘቡ ስላላቸው ብቻ የተጠየቁትን ዋጋ መክፈል አነስተኛ ገቢ ባላቸው እና በችግረኞች ላይ ተጨማሪ ጫና በመፍጠር ለአጠቃላይ የኑሮ ውድነቱ ተዋናይ እየኾኑ ነው። በየደረጃው የሚገኙ የንግድ እና ገበያ ልማት ተቋምም ይህን ሕገ ወጥ ንግድ እና የኑሮ ውድነትን የሚያባብስ ተግባር ለመከላከልም ለመቆጣጠርም ሲሞክር አይታይም።

በየጊዜው በሚፈጠሩ ችግሮች ሰበብ ምርት እየደበቁ አገልግሎት እየነፈጉ ዋጋ በመጨመር ለመክበር የሚዘርፉት አካላት ተው የሚላቸው አካል ሊኖር ግድ ይላል። ሠርቶ እና ለሀገር እሴት ጨምሮ ከሚገኝ ድሎት ይልቅ በዝርፊያ እና በሕዝብ ስቃይ ላይ የሚሰበሰብ ንዋይ የህሊናም የአካልም ምቾት አይሰጥም። ፍትኃዊ ባልኾነ መንገድ የተሰበሰበ ሃብት በሰላም ጊዜም በሕግ ከማስጠየቅ በሰላም እጦት ጊዜም ተመልሶ ከመዘረፍ አያመልጥም። እናም ባለነዳጆቻችን ሌላው ችግር ሳያንስ ነዳጅን በመደበቅ እና በሕገ ወጥ መንገድ በመቸርቸር ሕዝቡን ከማንገላታት ብትታቀቡስ። የመንግሥት አካላትም ሕግን በማስከበር ኀላፊነታችሁን ብትወጡስ እንላለን።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምሥጋና 🙏
Next articleዘመናዊ የመሬት መረጃ ሥርዓት በደብረ ብርሃን ከተማ እየተሠራ ነው።