
ባሕር ዳር: መጋቢት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሥነ ጽሑፍ መድረኮች ሁሉ ስሙ ይጠራል። ስሙ ተደጋግሞ የሚጠራበት ምክንያት ደግሞ የሥነ ጽሑፍ አብዮትን በማቀጣጠሉ ነበር።
የሥነ ጽሑፍ አብዮተኛው ዳኛቸው ወርቁን በአጻጻፉ ብቻ ሳይኾን በግለሰባዊ ባህሪውም ፈላስፋ ነው ይባላል። ከዘመኑ ቀድሞ የሚያስብ ነው።
ዳኛቸው ወርቁ የሚደነቅበት እና የሚታወስበት ምክንያት፤ በዚያ የፊውዳል ዘመን፣ በዚያ ወግ አጥባቂ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ፣ በዚያ ልማዳዊ ነገሮች አይነኬ በኾኑበት ዘመን ውስጥ ኾኖ “አደፍርስ” የተባለ ገጸ ባህሪ ፈጥሮ አዲስ የባሕል እና የፖለቲካ አብዮት መቀስቀሱ ነው።
አደፍርስ የመጽሐፉ ስም ሲኾን ዋና ገጸ ባህሪው አደፍርስ የተባለው ተራማጅ አስተሳሰብ የያዘ ፈላስፋ ነው።
ዳኛቸው የተወለደው በ1928 ዓ.ም ነው። አባቱ አቶ ወርቁ ለዘመናዊ ትምህርት ከፍ ያለ ግምት የሚሰጡ ነበሩ። ከ1936 ዓ.ም እስከ 1942 ዓ.ም ድረስ በተወለደበት አካባቢ፣ በደብረ ሲና አብዬ ትምህርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታተለ። ዳኛቸው በ13 ዓመቱ በዚህ ሳምንት “ያላቻ ጋብቻ ትርፉ ሐዘን ብቻ” የተሰኘች ተውኔት ደርሶ በመተወን ብቃቱን አሳይቷል። ሥራውን የጀመረው በዚሁ ነበር፡፡
በ1943 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በማቅናት በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እንዲሁም በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤቶች ተምሯል።
ዳኛቸው ወደ ደብረ ብርሃን ተመልሶ “ሰው አለ ብዬ” የተሰኘውን ተውኔቱን ጽፏል፡፡ ተውኔቱ የታተመውም በ1950 ዓ.ም ነው። ዳኛቸው በመምህርነት ሥልጠና ወስዶ በመመረቅ በአዲስ አበባ እና በሐረር አስተምሯል። በዚህ ጊዜም “ሰቀቀንሽ እሣት” የተሰኘ ትያትር ደርሶ እንዲታይ አደረገ። በተለያዩ ጋዜጦች ላይም ስላነበባቸው መጻሕፍት ምልከታዎቹን ለማስነበብ በቃ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ ለማስተማር ሲወስን፤ ዳኛቸው ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች መካከል አንዱ ኾነ። በ1953 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን መማር ጀመረ። የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ በዩኒቨርሲቲው በረዳት መምህርነት አገልግሏል።
ከዩኒቨርሲቲው ተመርቆ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በወቅቱ የተማሪው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ ከዘመነኞቹ የኮሌጁ ገጣሚዎች ከነታምሩ ፈይሳ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ አበበ ወርቄ፣ ይልማ ከበደ፣ ኢብሳ ጉተማ፣ ኃይሉ ገብረዮሐንስ፣ መስፍን ሃብተማርያም ጋር እንደ “ወጣቱ ፈላስማ” በመሳሰሉ ግጥሞቹ የለውጥ ሃሳቡን ያስተጋባ ገጣሚም ነበር።
በ1956 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ ከ1957 ዓ.ም እስከ 1961 ዓ.ም ድረስ በዚያው ዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት ያገለገለ ሲሆን “ትበልጭ” የተሰኘ ተውኔት ጽፎ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ለመድረክ አብቅቷል። በመቀጠልም ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አሜሪካ አቀና። በ1962 ዓ.ም. በአሜሪካ ኦሃዮ ዩኒቨርሲቲ “የፈጠራ ሥነ ጽሑፍ አጥንቶ በመመረቅ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ” የሚል ማዕረግ አገኘ።
ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ እስከ 1965 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ መምህርነት አገለገለ። ዳኛቸው “የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍልን” ያደራጀ እንዲሁም ወጣት የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎችን በማፍራት አስተዋጽዖ ያደረገ ምሁር ነው።
ዳኛቸው ባነሳቸው በሳል የለውጥ ሃሳቦች እና የተራቀቀ ሥነ ጽሑፋዊ የአቀራረብ ስልት የተደነቀውን፣ የኢትዮጵያን የዘመናዊ ልብ ወለድ ሥነ ጽሑፍ በእድገት ምዕራፍ ያሸጋገረውን እና “አደፍርስ” የተሰኘውን ልብ ወለድ መጽሐፉን በ1962 ዓ.ም በማሳተም ታላቅ ጠቢብነቱን አስመስክሯል።
የዳኛቸው ወርቁ ሌላው ሥራ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደርሶት እንግሊዝ ሀገር የታተመው እና “The Thirteenth Sun” የተሰኘው መጽሐፍ ነው። ይህ ሥራው በብዙ የአውሮፓውያን ቋንቋዎች ተተርጉሞ ታትሟል።
መጽሐፉ እስከ ዛሬ ድረስ በታላላቅ የምዕራባውያን የፈጠራ ጽሑፍ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በማስተማሪያነት እያገለገለ ይገኛል። ይህ ድርሰት የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ በዓለም አቀፍ መድረክ ያስተዋወቀ ሥራ ነው።
ዳኛቸው ከመጽሐፍቱ በተጨማሪ በወቅቱ ይታተሙ በነበሩት “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ”፣ “የኢትዮጵያ ድምጽ” እና “አዲስ ዘመን” ጋዜጦች ላይ የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ የተመለከቱ ሥራዎችን በማቅረብ እና የወጣት ደራሲያን ሥራዎችን በመሄስ ለሀገሪቱ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ምሁራዊ ኀላፊነቱን እና ተልዕኮውን ተወጥቷል።
ዳኛቸው የሀገሩን እምነት እና ባሕል ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ለሥራ ነገን የማያውቅ፣ ለውጥ ፈላጊ፣ ሀገር ወዳድ፣ ስለሀገር ኋላ ቀርነት ሁሌ የሚቆረቆር ዘርፈ ብዙ ባለሙያ እንደነበርም ይነገራል።
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣ
—–//////——/////—–/////——/////—–/////
በዛሬው የሳምንቱ በታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ “የንግድ ጄት” አብራሪ የኾኑትን ኢትዮጵያዊው ካፒቴን ዓለማየሁ አበበን እንቃኛለን።
ካፒቴን ዓለማየሁ ገና ከ10 ዓመታቸው ጀምሮ አውሮፕላን በሰማይ ላይ ሲበር ሲያዩ አውሮፕላን አብራሪ የመኾን ሕልም እንደነበራቸው በተለያዩ ጸሐፊያን የተሰነደው ታሪካቸው ያሳያል። ህልማቸውን ለማሳካት ጠንካራ ትጋት እና ሥነ ምግባር የነበራቸው ካፒቴን ዓለማየሁ በ1955 ዓ.ም የመጀመሪያውን “የንግድ ጄት” በማብረር በዘርፉ ፈር ቀዳጅ ኢትዮጵያዊ እንዲሁም አፍሪካዊ ለመኾን በቅተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ ወደ ጄት ዘመን ሲሸጋገር ከፋና ወጊ አብራሪዎች ተጠቃሹ ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ ነበሩ። የመጀመርያውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ቦይንግ 720B” አውሮፕላን በካፒቴንነት ያበረሩት ካፒቴን ዓለማየሁ፣ በዚሁ ተግባራቸው “የመጀመሪያው” አፍሪካዊም ናቸው። በ1955 ዓ.ም ቦይንግ ጄት ከሲያትል ቦይንግ ፋብሪካ አውሮፕላኑን እንዲያመጡ የተደረጉት ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ እና ካፒቴን አዳሙ መድኃኔ ነበሩ።
ካፒቴን ዓለማየሁ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመቀላቀል የቻሉት በኢትዮጵያ አየር ኃይል በኩል በማለፍ ነበር። በወቅቱ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ አቪዬሽን ትምህርት እንዲገቡ ሲደረግ ከዕድሉ ተጠቃሚዎች መካከል አንዱ ካፒቴን ዓለማየሁ ነበሩ። በ1943 ዓ.ም ምርጥ የሆኑ አብራሪዎች ከአየር ኃይል ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲዛወሩ በተወሰነው መሠረት ካፒቴን ዓለማየሁ ከተመራጮቹ አንዱ ኾነው የኢትዮጵያ አየር መንገድን በዚህ ሳምንት ተቀላቀሉ።
በሦስት አስርታት ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገልግሎት ዘመናቸውም ከመጀመርያ የበረራ መኰንንነት እስከ ካፒቴንነት እንዲሁም እስከ አየር መንገዱ የበረራ ዘርፍ ምክትል እና ዋና ኀላፊነት (ከ1948 እስከ 1960 ዓ.ም) ድረስ ሠርተዋል። ከ1961 እስከ 1972 ዓ.ም ደግሞ የዓለም አቀፍ በረራዎች ዳይሬክተር፣ የበረራ ኦፕሬሽን ረዳት ጄኔራል ማኔጀር ኾነው አገልግለዋል። በ1968 ዓ.ም. የመጀመርያው አፍሪካዊ የቦይንግ 707 ጄት ካፒቴን ኾነው ሲሾሙ፤ በ1972 ዓ.ም የጄት ካፒቴኖች ፈታኝ በመኾን አገልግለዋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አገልግሎታቸውን በ1974 ዓ.ም ፈጽመው ከተሰናበቱ በኋላ በኡጋንዳ እና በየመን አየር መንገዶች ውስጥ በአሠልጣኝነት እና በአማካሪነት ለአምስት ዓመታት ያህል ሰርተው የበረራ ምዕራፋቸውን ቋጭተዋል።
ምንጭ፡- በ1997 ዓ.ም ‹‹ሕይወቴ በምድርና በአየር›› በሚል ያሳተሙት መጽሐፍ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!