በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ከወከላቸው ሕዝብ ጋር ተገናኝተው እንዳይወያዩ እንዳገዳቸው የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ገለጹ።

12

ባሕር ዳር: መጋቢት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በሁሉም አካባቢዎች ተገኝተው ሕዝቡን ለማወያየት ቢቸገሩም የምክር ቤት አባላቱ በተለያዩ ዘዴዎች ከሕዝብ የተሰበሰቡ ጥያቄዎችን ለክልሉ ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ አቅርበዋል።

በክልሉ ከባለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ በይደር የነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎች ጋር ተዳምሮ ሕዝቡን ችግር ውስጥ እየከተተው መኾኑን የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ገልጸዋል።

በተለይም የፀጥታ ችግሩ በግብርና፣ በመሰረተ ልማት፣ በትምህርት እና በጤናው ዘርፍ እንዲኹም በኑሮ ውድነቱ ላይ ዳፋው እንዲበረታ አድርጎታል ነው ያሉት።

በግብርናው ዘርፍ የማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ ለማድረስ ከመቸገር በላይ ያለፈው ዓመት የአርሶ አደሮች የማዳበሪያ ድጎማ አለመከፈሉ የሕዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ የተጀመሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች በወቅቱ አለመጠናቀቅ እና በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ወራጅ ወንዞች በጥናት የተደገፈ የመስኖ አገልግሎት አለመስጠት እንደ ችግር ተነስቷል።

በትምህርት ዘርፉ በፀጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች ከመኖራቸው በተጨማሪ ተቋማቱ ከፍተኛ ውድመት እየደረሰባቸው ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ሌሎች የክልሉ ትምህርት ቤቶች የግብዓት አቅርቦት ችግር እና የትምህር ቤቶች የጥራት ደረጃ መውረድም የሕዝብ ጥያቄ ኾኖ ተነስቷል።

በመሰረተ ልማት ዘርፍ በተለይም የመንገድ፣ የመብራት እና የመጠጥ ውኃ አገልግሎት የክልሉ ሕዝብ ያልተፈቱ ጥያቄዎች ሲኾኑ የሰላም እጦት መኖሩ ደግሞ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል ነው ያሉት የተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ።

ከሕዝብ ከተሰበሰቡ ጥያቄዎች መካከል የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት በየጊዜው እየናረ መምጣት ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማኅበረሰብ እየፈተ ነው ብለዋል።

ይህ ሀገራዊ ችግር ቢኾንም በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ደግሞ በተለይም ሕገወጥ ነጋዴዎች እንዲበራከቱ እና መሰረታዊ ፍጆታዎች በአግባቡ ለሕዝቡ እንዳይዳረስ ምክንያት መኾኑም ተነስቷል።

በተነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች ላይም የክልሉ የተለያዩ የዘርፉ ቢሮ ኀላፊዎች ምላሽ ሰጥተውባቸዋል።

ለተነሱ ጥያቄዎችና ማብራሪያዎች በቀጣይ ዜና እንመለሳለን።

ዘጋቢ፡- አደራው ምንውየለት

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ክልል የሕዝብ ተወካዮች አባላት ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጋር በክልሉ ጉዳይ ውይይት እያደረጉ ነው።
Next articleየሥነ ጽሑፍ አብዮተኛው