በክልሉ መንግሥት ድጋፍ በወረዳው በተለያዩ ተቋማት ላይ የተከናወኑ የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መኾናቸውን የአዳርቃይ ወረዳ አሥተዳደር ገለጸ።

38

ደባርቅ: መጋቢት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሰሜን ጎንደር ዞን በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል ይጠቀሳል። አዳርቃይ ደግሞ ከፍተኛ ዘረፋና ውድመት የተፈጸመበት ወረዳ መኾኑ ይታወሳል።

የአማራ ክልል መንግሥት ጥር 2015 ዓ.ም 100 ሚሊዮን ብር በመበጀት በዞኑ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጡ ይታወሳል። ከዚህ በጀት ውስጥ 60 በመቶው ከፍተኛ ውድመት ለተፈጸመበት አዳርቃይ ወረዳ ነበር የተበጀተው። ወረዳው ከክልሉ መንግሥት ያገኘውን የገንዘብ ድጋፍ ተጠቅሞም በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን አከናውኗል። መልሶ ግንባታው ከተከናወነባቸው መካከል የአዳርቃይ ማይተክሊት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠቃሽ ነው። የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ብርሃኑ እሸቱ ትምህርት ቤቱ በ1987 ዓ.ም እንደተመሠረተ ነግረውናል።

ከጦርነቱ በፊት ትምህርት ቤቱ በግብዓት የተሻለ እንደነበርም አንስተዋል። ይሁንና በጦርነቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመውደሙ ለመማር ማስተማር ሥራ አስቸጋሪ ኾኖ መቆየቱን አውስተዋል። ርእሰ መምህሩ በትምህርት ቤቱ በተከናወነው የመልሶ ግንባታ ሥራ ሦስት ብሎኮች በመገንባታቸው ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል። በትምህርት ቤቱ የመምህራን ማረፊያ፣ ቢሮ፣ ቤተ መጽሐፍት እና መሰል ግንባታዎች ተገንብተዋል ያሉት ርእሰ መምህሩ የግብዓት ማሟላት ግን ይቀራቸዋል ነው ያሉት።

ተማሪ ሳሙኤል ከበበው እና ራሄል ተወልደ የአራተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ተማሪዎቹ ከዚህ ቀደም ይማሩበት የነበረው ክፍል ጣራ እና ግድግዳው የፈረሰ ስለነበር በፀሐይ እና በአፈር ምክንያት ለበሽታ ይጋለጡ እንደነበር ተናግረዋል። በዚህም ከትምህርት ገበታ ለመቅረት ስንገደድ ነበርም ብለዋል። ተማሪዎቹ አሁን ላይ ደረጃውን በጠበቀ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተላቸው ከበሽታ ስጋት ነጻ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የተገነባው መማሪያ ክፍል ለሁሉም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የሚበቃ ባለመኾኑ አሁንም በፈራረሰ ክፍል ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች መኖራቸውን አንስተዋል። ተጨማሪ መማሪያ ክፍል ተገንብቶ ሌሎችም በምቾት እንዲማሩ ጠይቀዋል። የአዳርቃይ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሚሊዮን ታደሰ ማኅበረሰቡ ወደ ቀየው ከተመለሰበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 13 ወራት በወረዳው በርካታ የመሠረተ ልማት መልሶ ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል መልሶ ማቋቋም እና ፈንድ ጽሕፈት ቤት በተደረገው ድጋፍ በወረዳው ሁለት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና የዛሪማ ጤና ጣቢያ ማስፋፊያ ግንባታ፣ የወጣቶች ሥብዕና መገንቢያ እና የሥራ እና ሥልጠና ማዕከል ግንባታ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደኾኑ አሳውቀዋል። አቶ ሚሊዮን በክልሉ መንግሥት ከተከናወኑት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በተጨማሪ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን እገዛ ማድረጋቸውንም አንስተዋል።

በወረዳው በተለያዩ ተቋማት ላይ የተከናወኑት የመልሶ ግንባታ ሥራዎችም ማኅበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ እድል የፈጠሩ መኾናቸውን አሥተዳዳሪው ጠቁመዋል። በግንባታ በኩል ለተከናወኑት ሥራዎች ምሥጋና ያቀረቡት አሥተዳዳሪው በሌሎች ተቋማትም ላይተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባልም ብለዋል።

ከግንባታ ባሻገር በተለይም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ላይ ያለው የግብዓት እጥረት ለአገልግሎት አሠጣጥ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ በመኾኑ መንግሥት እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኢትዮጰያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል እና ከአባል አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ጋር ተወያዩ።
Next articleበሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ክልል የሕዝብ ተወካዮች አባላት ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጋር በክልሉ ጉዳይ ውይይት እያደረጉ ነው።