
አዲስ አበባ: መጋቢት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)እንደ ሀገር መግባባት ላይ ባልተዳረሰባቸው መሠረታዊ ጉዳዩች ላይ ምክክር በማድረግ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል መተማመን ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት እየሠራ መኾኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል። ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እና ለመጪው ትውልድ ጠንካራ መሠረት ያለው ሀገር ለማስረከብ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ተገልጿል።
ኮሚሽኑ የአጀንዳ አሠባሠብ፣ ምክክር እና ለሀገራዊ ጉባኤ የተወካዮች የልየታ አሠራር ሥርዓትን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እና የግብዓት ማሠባሠቢያ መድረክ እያካሄደ ነው።
የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በመክፈቻ ንግግራቸው ምክክሩ አሳታፊ፣ ግልጽ እና ኅብረተሰቡ የኮሚሽኑን ተግባር እና ኀላፊነት እንዲያውቅ ከቅድመ ዝግጅት ሥራው ጀምሮ መሥራታቸውን ገልጸዋል።
ችግሮችን ለመፍታት ምክክርን ብቻ አማራጭ ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።
ኢትዮጵያን የሚመስል አካታች ብዝኃነትን የሚያሳይ ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ ሁሉም ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!