የውይይት መድረኮቹ ሕዝቡ ለሀገረ መንግሥቱ ቀጣይነት ያለውን ዝግጁነት እና ቁርጠኛ አቋም ያንጸባረቀባቸው መኾናቸውን ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ገለጹ።

42

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ባለፉት ሳምንታት ስኬታማ የሕዝብ ውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሚሄድ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ጥቅሞች እና ፍላጎቶች ውስጥ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፡፡ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ዜጎች በሀገራቸዉ በሚታዩ በመሠረታዊ ችግሮቻቸው እና በመፍትሔዎቻቸዉ ዙሪያ ግንዛቤያቸው እንዲያድግ፣ የተለያዩ ወገኖች ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹ እና ድምጻቸውን ለማሰማት እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል፡፡

በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት፣ የተለያዩ ፍላጎቶችን ለማጣጣም እና ለግጭት አፈታት አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚችሉም አመላክተዋል፡፡ በተለይም ለሁሉም ክፍት የኾኑ፣ አሳታፊ፣ አካታች እና የተለያዩ አመለካከት የሚራመድባቸው የውይይት መድረኮች ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ አብሮነት እና ትብብርን በማጎልበት በኅብረተሰቡ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቡድኖች መካከል መተማመንን ያበረታታሉ፣ ይፈጥራሉ ነው ያሉት፡፡

በአንድ ሀገር ባሉ ማኅበረሰቦች መካከል ለትብብር፣ ለመረዳዳት እና የጋራ መግባባት ለመፍጠር መተማመን አስፈላጊ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ መግባባት እና መተማመን ሀገረ መንግሥቱንም ኾነ የሀገር ግንባታ ሂደቱን ዘላቂ መሰረት እንዲኖረዉ ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡ ሕዝባዊ ውይይቶች የተለያዩ ማኅበረሰቦች በዉስጣቸዉ ያለዉን ውጥረት እንዲያረግቡ፣ የጋራ መግባባት እንዲፈጥሩ እና በሰላም አብሮ ለመኖር እንዲሠሩ ያስችላቸዋል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሀገሪቱ ከሚገኙ ክልሎች ከተዉጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ያካሄዷቸው እና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በሀገሪቱ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች፣ ያደረጓቸው ውይይቶች መሠረታዊ መርኾዎችን ለማሳካት ያለሙ እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡ ሕዝባዊ የዉይይት መድረኮቹ በሁለቱ ከተማ አሥተዳዳሮች እና በክልሎች እና ከ70 ባላነሱ ዋናዋና ከተሞች መካሄዳቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በየከተሞች የአንዱ ክልል መሪ ወደ ሌሎች ክልል ከተሞች በመመደብ ከፌዴራል ከፍተኛ መሪዎች ጋር በቅንጅት የተካሄደ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ በውይይቱ ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር በጋራ ጉዳዮች ለመወያያት የነበረዉ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት፣ ጥያቄዎቹን ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ በኾነ መልኩ ያነሳበት፣ ለተሠሩ ሥራዎች እውቅና የሰጠበት እና ቀጣይነት እንዲኖራቸዉ ፍላጎቱን የገለጸበት፣ መሪዎችንም ያበረታታበት፣ ጉድለቶችንም መንግሥት እንዲያርም በነፃነት ያነሳበት ነበር ብለዋል፡፡

የተጀመሩ የለዉጥ ሥራዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩ ፍላጎቱን የገለጸበት፣ ለሰላሙም ኾነ ለልማቱ ከፍተኛውን ድርሻ በመወጣት “እዳን ወደ ምንዳ” ለመቀየር በከፍተኛ ተነሳሽነት እና በቁጭት ለመሥራት፣ ሃብት ለመፍጠር እና የወል ትርክት ላይ በማተኮር ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ ዝግጁነቱን ያረጋጋጠበት እንደነበርም አመላክተዋል፡፡

ለከፍተኛ መሪዎችም የሕዝቡን የመልማት ፍላጎቶች፣ እንዲቀረፉ የሚፈልጋቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች የተረዱበት፣ አንዱ የሌላዉን አካባቢ ችግሮች እና ህመሞች መገንዘብ እንዲችል እድል ያገኙበት፣ ተገቢዉን ልምድ እና ግንዛቤ የፈጠሩላቸው ነበሩም ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ከሰላም እና መረጋጋት፣ ከኑሮ ዉድነት፣ የሥራ እድል ፈጠራ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በስፋት ያነሳበት፣ በተነሱ ጉዳዮች እና ችግሮች አፈታት ማን ምን መሥራት እንዳለበት የጋራ መግባባት የተፈጠረበት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ለልማት በዕቅድ የተያዙ፣ በቂ በጀትም የተመደበላቸው እና በአሥተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት በወጉ ያልተፈጸሙ መሠረታዊ ችግሮች ለይቶ በፍጥነት መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡ በበጀት እጥረት ምክንያት ያልተፈጸሙ ልማቶችንም ኅብረተሰቡን በማስተባበር፣ ከአጋር አካላት ሃብት በማፈላለግ እና ልዩ ልዩ የፈጠራ መንገዶችን በመጠቀም መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡

በእቅድ ያልተያዙ፣ ሰፊ ሃብት እና ጊዜ የሚጠይቁ ከማልማት እና በፍጥነት ለመበልጸግ ከመፈለግ የተነሱ ጉዳዮችን በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ እቅድ ውስጥ በማካታት በቅደም ተከተል መፍታትን እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡ ከዘላቂ እና አዎንታዊ ሰላም፣ ሕግ ማስከበር፣ ሕገ ወጥነትን መከለከል ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በመንግሥት የተከፈተዉን የሰላም በር ኅብረተሰቡን ባሳተፈና ከፍተኛ ድርሻውን መወጣት በሚችል አኳኋን መፍታት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡ በዚህ መፍታት ያልተቻለዉን ደግሞ ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ በማያደግም ሁኔታ ችግሩን መቅረፍ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ከመልካም አሥተዳደር ጋር ተያይዘው የተነሱ ጉዳዮችን አሠራሮችን በማዘመን በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የውይይት መድረኮቹ ሕዝብ የተጀመረዉን ሁሉን አቀፍ ለውጥ እና የለዉጡን ሥርዓት ለማስቀጠል የበኩሉን ሚና በመወጣት ለሀገረ መንግሥቱ ቀጣይነት ያለውን ዝግጁነት እና ቁርጠኛ አቋም ያንጸባረቀበት እንደነበሩም ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት አስታውቀዋል፡፡ ሕዝባዊ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ማረጋገጣቸውንም ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የሚንስትሮች ምክር ቤት ሕዝብ የሚያነሳቸው ጉዳዮች ተነስተው እንዲፈቱ እና የሚመለከተቸው ተቋማት በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ እቅዳቸዉ እንዲያካትቱ አቅጣጫ መቀመጡንም አስታውቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጽንፈኛው ላይ እየተወሰደ ያለው ጠንከር ያለ እርምጃ ተደራጅቶ የመዋጋት አቅሙን እንዲያጣ አድርጎታል” ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ
Next articleእንደ ሀገር መግባባት ላይ ባልተደረሰባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ በመተማመን ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት እየሠራ መኾኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ