“በጽንፈኛው ላይ እየተወሰደ ያለው ጠንከር ያለ እርምጃ ተደራጅቶ የመዋጋት አቅሙን እንዲያጣ አድርጎታል” ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ

80

ባሕር ዳር: መጋቢት 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር የማፍረስ ተልዕኮን አንግቦ የአማራ ክልልን የጽንፈኞች ማዕከል ለማድረግ ነፍጥ አንግቦ የዘረፋ ተግባር በሚፈጽመው ጽንፈኛ ላይ እየተወሰዱ ያሉ አርምጃዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የባሕር ዳር እና ጎንደር ኮማንድፖስት ሰብሳቢ እና የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ተናግረዋል።

የኮማንድፖስቱ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ከጎንደር እና ባሕር ዳር ዙሪያ ከወረዳ እና ከዞን ለተውጣጡ አመራሮች የከላስተሩን ወቅታዊ ሁኔታ እና በቀጣይነት በኮማንድፖስቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ገለፃ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። በጽንፈኛው ላይ እየተወሰደ ባለው ጠንከር ያለ እርምጃ ተደራጅቶ እና ቆሞ እንዳይዋጋ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ጽንፈኛው ቡድን በሰራዊታችን በደረሰበት ጠንካራ ምት እንዲሁም ራሱ ጽንፈኛው በኅብረተሰቡ ላይ በሚፈጸመው ግፍ እና በደል ከኅብረተሰቡ እንዲነጠል እና አቅሙን እንዲያጣ አድርጎታል ሲሉም ተናግረዋል። ሰራዊቱ ለክልሉ ሰላም መስፈን ሌት ተቀን በጽናት ዘብ ቆሟል ያሉት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ እና የኮማንድፖስቱ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ በቀጣይነትም የዘራፊውን ቡድን ስብስብ ለማጽዳት ጽንፈኛውን ሙሉ ለሙሉ ከሕዝቡ የመነጠል፣ ተከታታይነት ያለው ማጥቃት፣ ጠላት የገባበት ገብቶ የማሰስ፣ የመፈለግ እና እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል፤ በአጭር ጊዜ ተልዕኮውን አጠናቆ ለክልሉ ጸጥታ ኃይልም ያስረክባል ብለዋል።

በሰራዊቱ እና በክልሉ የፀጥታ ኃይል ተልዕኳቸውን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ዞን እና ወረዳዎች ራሳቸውን ችለው የሚያስተዳድሩበትን እና አካባቢያቸውን መጠበቅ የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከእያንዳንዱ አመራር በቁርጠኝነት ወደ ሥራ መግባት እና በቅንጅት መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።

ጠላት ትላንት በነበረው ቁመና ላይ አይደለም ያለው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው ናቸው። ኀላፊው በአሁኑ ወቅት በክልሉ ጠንካራ የፀጥታ ኃይል መገንባቱን እና የፀጥታ ኃይሉን የሚመራም ጠንካራ የፖለቲካ አመራርም መፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የመከላከያ ሠራዊቱ ለሕዝባችን ሰላም የከፈለው መስዋዕትነትን ሁሌም የምናስታውሰው ነው። የክልላችንን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስም ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ ነን፤ የኮማንድፖስቱ ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል ሲል የመከላከያ ሰራዊት አስታውቋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቤት ሠራተኞችን መብት የሚያስከብር ሕግ እንዲወጣ የአማራ ክልል የቤት ሠራተኞች ማኅበር ኅብረት ጠየቀ።
Next articleየውይይት መድረኮቹ ሕዝቡ ለሀገረ መንግሥቱ ቀጣይነት ያለውን ዝግጁነት እና ቁርጠኛ አቋም ያንጸባረቀባቸው መኾናቸውን ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ገለጹ።