
ባሕር ዳር: መጋቢት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ትንሳኤ የአማራ ክልል የቤት ሠራተኞች ማኅበር ኅብረት ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በፓናል ውይይት አክብሯል።
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ማርች 8 ሴቶች መብታችንን ለማስከበር የተነሳንበት ነው ብለዋል። በዓሉን ስናከብር የሴቶች መብት እና ጥቅም እየተከበረ ስለመኾኑ መጠየቅ እና ተባብሮ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። በዓሉን ስናከብርም ለጥቃት የተጋለጠችውን፣ እኩል ክፍያ ያጣችውን እና መብቷን የተነፈገችውን ሴት አስቦ ለመሥራት መኾን እንዳለበት አሳስበዋል።
የአማራ ክልል የቤት ሠራተኞች ማኅበር ኅብረት ፕሬዚዳንት ባንቻዬ ተፈራ ከአስር ዓመት በፊት የቤት ሠራተኝነትን ጀምራለች። የማታ ትምህርት ጀምራ እስከ 12ኛ ክፍል አጠናቅቃለች። አሁን ላይም የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች። ይህን ሁሉ ያሳካችው በቤት ሠራተኝነት ሕይወት ውስጥ ኾና ነው። ባንቻዬ እስካሁንም ማኅበረሰቡ ለቤት ሠራተኝነት ያለው አመለካከት የተሳሳተ መኾኑን ገልጻለች። ደመወዛቸውን የሚቀሙ፣ ለጾታዊ ጥቃት የሚጋለጡ፣ እና ሌሎች በደሎች የሚደርሱባቸው ሴቶች መኖራቸውን ጠቅሳ ይህም በማኅበር ተደራጅታ ለመታገል እንዳነሳሳት ተናግራለች። ሲ. ቪ. ኤም በሚባል ድርጅት አማካኝነት በ40 አባላት የቤት ሠራተኞች ማኅበርን ማቋቋማቸውን ጠቅሳለች። ለመብታቸው እየታገሉ እንደኾነ ተናግራለች።
በማኅበር መደራጀታቸው በራሱ ስኬት መኾኑን የጠቀሰችው ባንቻዬ የቤት ሠራተኞችን መብት ለማስከበር ማኅበራቸው እየሠራ መኾኑን ገልጻለች። ማኅበሩ በሀገር አቀፍ ደረጃም ተጠናክሮ መብትና ጥቅሞቻቸው እንዲከበሩ፣ ዓለም አቀፍ ድንጋጌን የሚተገብር ክልላዊ ሕግ መረቀቁን ጠቅሳለች።
የአንድነት የቤት ሠራተኞች ማኅበር አባል እሌኒ ጓዴ በበኩሏ ማኅበራቸው የቤት ሠራተኛ ሴቶችን በማደራጀት እና የመብት ጥሰት በሚፈጸምባት ላይም መብቷን በሕግ በማስከበርም ኾነ በማስማማት እንደሚሠራ ገልጻለች። እርስ በርሳቸው በመማማር እና ከአሠሪዎቻቸው ጋር የቅጥር ውል ይዘው በመሥራት መብቶቻቸውን ለማስከበር እየታገሉ እንደኾነ ገልጻለች። እንደማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ሕግ እና ደንብ ወጥቶልን መብት እና ጥቅማችን እንዲከበር መንግሥትን እና የሚመለከተውን አካል እየጠየቅን ነው ብላለች። ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት ያወጣው ድንጋጌ በኢትዮጵያ እንዲከበር እየጠየቁ እንደኾነም ገልጻለች።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ የሥራ ሥምሪት ማስፋፊያ ቡድን መሪ ዘውዱ ደሳለኝ በኢትዮጵያ የቤት ሠራተኞች ጉዳይ ገና ልዩ ሕግ እንዳልወጣለት ጠቅሰው የመደራጀት መብታቸውን በመጠቀም እንደ ውጪ ሀገር የሥራ ስምሪቱ ለሀገር ውስጥ ሠራተኞችም ልዩ አዋጅ እንዲወጣላቸው እየታገሉ መኾኑን ገልጸዋል። የዓለም የሥራ ድርጅት ሥምምነት 189 እንዲጸድቅ እና በአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156/ 2011 መሠረት ደንብ እንዲወጣ እየጠየቁ መኾኑን ተናግረዋል። ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የየደረጃው ተቋማትም መብታቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት ጥረት እገዛ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፍ ስምምነትን ማጽደቅ የሚቻለው በሀገር ደረጃ መኾኑን የጠቀሱት አቶ ዘውዱ ለጊዜው ግን በክልል ደረጃ የተዘጋጀ የውል ሰነድን ኤጀንሲዎች እና ሠራተኞች እንዲጠቀሙ እየተደረገ መኾኑን አመላክተዋል። የቤት ሠራተኞች ማኅበርም ቤት ለቤት በመዞር ትምህርት እየሰጡ መኾኑን ነው የገለጹት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!