ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ አሰባሰብ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ ውይይት እያካሄደ ነው።

39

ባሕር ዳር: መጋቢት 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአጀንዳ አሰባሰብ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው። በውይይት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዳሉት ሀገራዊ ምክክር መግባባት ላይ ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች መግባባት ላይ እንዲደረስ እየሠራ ይገኛል።

በዚህም ኢትዮጵያውያን ተወያይተው የጋራ መፍትሔ እንዲያስቀምጡ እየተሠራ መኾኑን አስታውቀዋል።
ኮሚሽኑ በወረዳዎች ደረጃ ሲያከናውን የቆየውን የተሳታፊ ልየታ ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክር ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታላቅ መሠረት የሚጥል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ አሁን ላይ ወደ ተግባር ምዕራፍ እየገባ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ለምክክሩ ወሳኝ እና ተከታታይ የኾኑ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ገልጸው፤ ለዚህም በርካታ ተባባሪ አካላት መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ምክክር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች መሰጠታቸውንም አስታውቀዋል።
የሀገራዊ የምክክር ሂደት ለትውልድ የምትመች ሀገር ለማስተላለፍ እንደሚረዳም ጠቁመዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደት ማስጀመሪያ የአሠራር ሥርዓት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው ብለዋል።
እየተካሄደ በሚገኘው የውይይት መድረክ ሚኒስትሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ከሁሉም ክልሎች የተወከሉ ባለድርሻ አካላት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዛሬ ከሰዓት በኋላ የኡጋንዳ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ካጉታ ሙሴቬኒን መልዕክት ለማድረስ የመጡትን የኡጋንዳ የፍትህና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ሚኒስትር የተከበሩ ኖበርት ማኦን ተቀብያለሁ። በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይም ውይይት አድርገናል።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየቤት ሠራተኞችን መብት የሚያስከብር ሕግ እንዲወጣ የአማራ ክልል የቤት ሠራተኞች ማኅበር ኅብረት ጠየቀ።