ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከፌዴራል የሱፐርቪዥን ቡድን አባላት ጋር ተወያዩ፡፡

64

ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ የተመራ የፌዴራል መንግሥት የሱፐርቪዥን ቡድን ባሕር ዳር ገብቷል፡፡ ቡድኑ በቆይታው ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር እየመከረ ነው፡፡

ሚኒስትሯ እንደገለጹት የሱፐርቪዥን ቡድኑ በቆይታው የክልሉን የሰላም፣ የልማት፣ የዴሞክራሲ እና ሌሎች አገልግሎቶችን አፈጻጸም በሚመለከት ነው የሚወያየው፡፡ በሌሎች ክልሎችም ተመሳሳይ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት የሱፐርቪዥን ቡድን በውይይቱ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት አፈጻጸሞችን ይመለከታል፣ ያጋጠሙ ችግሮችን የጋራ ያደርጋል፤ በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እና እገዛ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ዙሪያ ግብዓት ይይዛል ብለዋል፡፡

የሱፐርቪዥን ቡድኑ በክልሉ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማኅበራዊ እና መሰል አፈጻጸሞች ላይ ትኩረት አድርጎ ይወያያል። ሰላምን ማረጋገጥ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የድርቅ ተጋላጭነትን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ የገበታ ለሀገር የጎርጎራ ፕሮጀክት አፈጻጸም፣ የከተማ እና መሠረተ ልማት፣ የገቢ አሰባሰብ፣ መሬት አሥተዳደር፣ ማዕድን፣ የሥራ እድል ፈጠራ እና ሌሎች አፈጻጸሞች የውይይቱ አካል ናቸው ተብሏል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ መርሐ ግብር ተጀመረ።
Next articleበከተሞች የሚገነቡ የመሠረተ ልማት ተቋማትን በተቀናጀ መንገድ እንዲከናወኑ ትኩረት መደረጉን አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ገለጹ።