ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ መርሐ ግብር ተጀመረ።

24

ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ(ኮምፖነንት 3 ነጥብ 2) የተሰኘ መርሐ ግብር ተጀምሯል።

መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ በዓለም ባንክ እና በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትብብር የተዘጋጀ መኾኑም ተነግሯል። በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የዓለም ባንክ፣ የባንክ እና የፋይናንስ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ጌታቸው ዋቄ መርሐ ግብሩ በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ቅንጅት የሚተገበር ነው ብለዋል። መርሐ ግብሩ በዋናነት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ባልኾኑ አካባቢዎች የኃይል ተደራሽነት እንዲኖር ለማድረግ ያለመ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ኢዜአ እንደዘገበው የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ደግሞ ሌላኛው ትኩረቱ ነው ብለዋል።

በ42 ሚሊዮን ዶላር የሚካሄደው ይኸው መርሐ ግብር ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መኾኑም በመድረኩ ተገልጿል። መርሐ ግብሩ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2021 ጀምሮ ሲተገበር የቆየው ያልተማከለ የኤሌክትሪክ ኃይል እና መብራት አቅርቦት ፕሮጀክት አካል መኾኑም ተመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሁመራ ከተማ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን ገለጹ።
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከፌዴራል የሱፐርቪዥን ቡድን አባላት ጋር ተወያዩ፡፡