
ሁመራ: መጋቢት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በ2016 የምርት ዘመን 3 ሺህ 750 ሄክታር መሬት በጊዜያዊ አትክልት በመስኖ እየለማ ይገኛል። በዚህ የመስኖ ልማት 2 ሺህ 960 አርሶ አደሮች ተሳታፊ ኾነዋል።
ወይዘሮ አሚና አብዱ እና አቶ ሞላ ፈንቴ በዞኑ የሁመራ ከተማ ነዋሪ ናቸው፤ በከተማ ግብርና በመስኖ ልማት ላይ ተሠማርተው ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ እና ሌሎች ጊዜያዊ ተክሎችን አምርተው ለኅብረተሰቡም ያቀርባሉ።
ምርታቸውን ለገቢያ በማቅረብ ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኙም አንስተዋል። በቀጣይ ምርቶቻቸውን በስፋት እና በጥራት ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚ ለመኾን በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የነዳጅ እና የማዳበሪያ ችግር እንዲቀረፍላቸውም ጠይቀዋል።በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሁመራ ከተማ አሥተዳደር ሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ሺፈራው በ2016 በጀት ዓመት ለ1ሺህ 142 ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ሲሠራ ቆይቷል፡፡
ኀላፊው በግማሽ በጀት ዓመት ለ1ሺህ 560 ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል።በመስኖ ልማት የሥራ እድል ከ400 በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩንም አስረድተዋል፡፡
በዚህም ምርቶቻቸውን ለማኀበረሰቡ በማቅረባቸው የገቢያ መረጋጋትን ፈጥሯል ነው ያሉት። በመስኖ ልማት ለተሠማሩ የነዳጅ እና የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ እያጋጠማቸው ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ :- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!