ከ2 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች በከተማ ግብርና የጓሮ አትክልት እንዲያለሙ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

25

ወልድያ: መጋቢት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመኖሪያ ቤት ግቢና በመንግሥታዊ ተቋማት የከተማ ግብርናን እያስፋፋ መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ደስታ ሰጠ ገልጸዋል።

በያዝነው ዓመት እስካሁን እያለሙ ካሉት ነዋሪዎች በተጨማሪ ከ2 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶችን ተደራሽ የሚያደርግ የዘርና የፍል አቅርቦት መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

መምሪያው ከዘርና ፍል አቅርቦት በተጨማሪ ለጓሮ አትክልት አልሚ የከተማ ነዋሪዎች የግብርና ባለሙያዎቹ የአትክልት እንክብካቤ እና ክትትል ላይ ትኩረት ያደረገ ድጋፍ እያደረጉ መኾኑን ነግረውናል።

የጓሮ አትክልት በማልማት እየተጠቀሙ ያሉ ነዋሪዎች በበኩላቸው አትክልት ጋር መዋል፣ አትክልትን መንከባከብ ተዝናኖትን ይፈጥራል ነው ያሉት። ከተዝናኖት ባለፈም የተመጣጠነ ምግብ ለመመገብ መቻላቸውንም አስገንዝበዋል። አሁን ላይ በጓሯቸው ቀይ ስር፣ ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ ድንች፣ ካሮት፣ ጎመንና መሰል የጓሮ አትክልቶችን እያለሙም ይገኛሉ፡፡ በጓሯቸው አትክልትን ማልማታቸው ወጫቸውን መቀነስ እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት።

ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕግ የማስከበር ኀላፊነት የወደቀው በአሥተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ተቋማት ትከሻ በመኾኑ ክፍተቶችን ለይቶ መሙላት እና ማስተካከልን ይጠይቃል” አቶ ደሳለኝ ጣሰው
Next articleየሁመራ ከተማ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መኾናቸውን ገለጹ።