
ባሕር ዳር: መጋቢት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ በተዋረድ የሚገኙ የምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችን እና የምክር ቤቶች ፎረም አሥተባባሪዎችን ትናንት ከሰዓት አወያይተዋል፡፡ በውይይቱ የበጀት ዓመቱ ያለፉ ወራት አፈጻጸሞች እና ያጋጠሙ ችግሮች ተነስተዋል፡፡
የምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎችም በውይይቱ የተሠሩ ሥራዎች እና ያጋጠሟቸውን ችግሮች አንስተዋል፡፡ ምክር ቤቶች የሕዝብ ውክልናቸውን ስለሚወጡበት ሁኔታ፣ በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ስለሚኖራቸው ኀላፊነትም ውይይት ተደርጓል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ምክር ቤቶች በሕግ የተሰጣቸውን ኀላፊነት ለመወጣት ሕዝቡ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ምክር ቤቶች እና አስፈጻሚ አካላት በየድርሻቸው ችግሮችን እንዲፈቱ ቁጥጥር እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ፋንቱ የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ መሻሻል እንዳለው እና በችግሩ ውስጥም ኾነው ምክር ቤቶች ካሏቸው ተግባራት አንጻር ምን እየሠሩ እንደነበር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ከቦታ ቦታ የአፈጻጸም ልዩነት ቢኖርም በእቅዳቸው መሠረት ተግባራቸውን የፈጸሙ የወረዳ ምክር ቤት አባላት መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በአማራ ክልል ለተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ምክር ቤቶችም ኀላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣት ድርሻ ያለው መኾኑን ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ጠቅሰዋል፡፡ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ኀላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸውም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሃይል የመናድ አጀንዳ ይዘው ለተነሱት ኀይሎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል፡፡
የሰላሙ ሁኔታ የበለጠ እንዲሻሻልም ምክር ቤቶች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል ምን ተግባር ፈጸምን በሚል ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ”በጽንፈኝነት እሳቤ በተፈጠረው የሰላም መታወክ በዋነኛነት እየተጎዳ ያለው ሕዝቡ ነው” ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ የተሳሳተው አመለካከት እና ተግባር ትውልድ ላይ በሚሠሩ ሥራዎችን ሳይቀር እያደናቀፈ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡
ስለዚህ ምክር ቤቶች በግንባር ቀደምነት ለሕዝቡ ተገቢውን መረጃ በመስጠት ለሰላሙ እንዲቆም ማድረግ እንዳለብን ተነጋግረናል ብለዋል፡፡ ተቋማዊ አሠራርን በማጠናከርም ችግሮችን መፍታት የሚችል አቅም መፍጠር እንደሚቻል ነው ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ የገለጹት፡፡ ለዚህም የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ እንዲሠራ ምክር ቤቶች መረጃ በመስጠት ሕዝቡን ማስገንዘብ አለባቸው ብለዋል፡፡
የሕዝብ ሰላም ካልተከበረ ምክር ቤት መኖሩ ውጤት እንዳልኾነም አንስተዋል፡፡ ምክር ቤቶችም በግንባር ቀደምነት በማሥተባበር የሕዝቡን ብዥታዎች በማጥራት ለሰላሙ እንዲቆም ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ምክር ቤቶች በአግባቡ እየተወያዩ ሰላምን እና ልማትን አስተሳስረው መምራት እና መቆጣጠር እንደሚጠቅባቸውም ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!