
ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ላለፉት ተከታታይ ሦስት ቀናት በክልሉ ርእሰ መዲና ባሕር ዳር “ቃልን በማክበር በዘላቂነት እግርን መትከል” በሚል መሪ መልእክት ሲካሄድ የነበረው የምክክር መድረክ ዘጠኝ ነጥቦች ያሉት የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቅቋል፡፡
በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ እና መካከለኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች የተሳተፉበት የምክክር መድረኩ አሁናዊውን ነባራዊ ሁኔታ የዳሰሰ ጥልቅ ውይይት እና ምክክር ተደርጎበታል ተብሏል፡፡
የክልሉን ሰላም እና ልማት በሚመለከት ውስጣዊ እና ውጫዊ እድሎችን፣ መልካም አጋጣሚዎችን እና ስጋቶችን የዳሰሰ እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡ክልሉ የገጠመው ቀውስ ሰፊ እና ውስብስብ ነበር ያሉት በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ችግሮቹን ፖለቲካዊ ብስለት እና ጥበብ ባለው መንገድ ካለፍናቸው እድልም ይዘው ይመጡ ይኾናል ነው ያሉት፡፡
ፈተናዎችን ወደ እድል ለመቀየር ደግሞ የውስጥ አሠራርን መፈተሽ እና ክፍተቱን የጋራ ማድረግ ያስፈልጋል፤ የምክክር መድረኩም ዓላማ ይሄ ነበር ብለዋል፡፡የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ግልጽ፣ ውለው ያደሩ እና መፈታት ያለባቸው ናቸው ያሉት አቶ አሸተ ጥያቄዎቹን በበሰለ መንገድ ለማስመለስ የሕዝብን ንቁ ተሳትፎ እንደሚፈልግ አስረድተዋል፡፡
በተበጣጠሱ ችግሮች የማይነጣጠል፣ ኀይል የሚያሠባሥብ እና ፈተናዎችን መጋፈጥ የሚችል ቁርጠኛ መሪ እና ተመሪ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ዘመናትን የተሻገረ ጥንታዊ የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ እና ልምድ ያለው ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡
ዋና አሥተዳዳሪው የገጠሙትን ወቅታዊ ችግሮች በብስለት ለመሻገር የሚያስችል አቅምም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በየደረጃው የሚገኘው የፖለቲካ አመራር ሕዝብን ፊት ለፊት አግኝቶ መነጋገር፣ መምከር እና የመውጫ መንገዶችን በጋራ መቀየስ ይገባል ብለዋል፡፡
በክልሉ የሚገኘው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራር በወቅታዊ ችግሮች ዙሪያ በጋራ መነጋገሩ ተቀራራቢ ግንዛቤ እና የማስፈጸም ቁርጠኝነት እንዲላበስ አድርጎታልም ነው ያሉት፡፡
አቶ አሸተ “የምክክር መድረኩ የሰመረ የመንግሥት እና የሕዝብ መስተጋብር ለመፍጠር የሚያስችል ግንዛቤ ተፈጥሮበታል” ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!