
ባሕርዳር: መጋቢት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “ለነገዋ” የሴቶች የተሀድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከልን መርቀው ከፍተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ፕሮጄክቱ እስካኹን ድረስ አዲስ አበባ ላይ ከተሠሩ ፕሮጄክቶች ሁሉ ድንቅ ነው ብለዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የታሪክ ስብራታችንን ለመጠገን በአፍሪካ ተወዳደሪ የማይገኝለት የዓድዋ ሙዚዬም መገንባት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በአዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክ፣ መስቀል አደባባይ እና ሌሎች ፕሮጄክቶች መገንባታቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሠሩት ሥራዎች እጅግ ድንቅ ናቸው ብለዋል፡፡ እስካሁን የተሠሩት ሥራዎች ግን ተደምረው “ለነገዋ” የሴቶች የተሀድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል አያክሉም ነው ያሉት፡፡
ፕሮጄክቱ እንደ ሀገር ያሉብንን ሁለት ስብራቶች ለመጠገን እድል ይሰጣል ብለዋል፡፡ አንደኛው ልጆች ወልደን፣ ተንከባክበን አስተምረን ለወግ ማዕረግ ማብቃት ሲገባን ባሉን ዘርፈ ብዙ ድካሞች ልጆቻችን ለጎዳና እና ለአልተገባ የሕይወት ዘይቤ ሲዳረጉ ቆተዋል፤ የእነርሱን ሕይወት ማቅናት እንደ ሀገር ያለውን ስብራት መጠገን እንደኾነም አስረድተዋል፡፡
በዓመት 10 ሺህ ሴቶችን ካሉበት የኑሮ ኹኔታ አውጥተን የተሻለ ሥራ ማስያዝ የምንችል ከኾነ 10 ማዕከል ብንገነባ በዓመት 100ሺህ ሴቶችን ከዚህ ሕይወት እንገላግላለን ነው ያሉት፡፡ አምስት ዓመት ጠንክሮ የሠራ ከንቲባ ግማሽ ሚሊዮን ሴት ካልተገባ ሕይወት እንደሚያወጣም አመላክተዋል፡፡
እስካኹን የሠራነው ሥራ ለሕዝባችን ቃል የገባነውን ነው፣ አኹን የሠራነው ሥራ ግን ለፈጣሪም ቃል የገባነውን ነው ብለዋል፡፡ ማዕከሉን ለሠሩ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ሁለተኛው እንደ ሀገር ያለብን ስብራት ስክነት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለው የስክነት ስብራት ማሰብ፣ ማስተዋል፣ የዕለቱን ሳይኾን አሻግሮ መመልከት እና ትውልድን ማዕከል አድርጎ ማሰብ እንዳይቻል ስለማድረጉ ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ዛሬ ስለሚወስደው ነገር እንጂ ነገን እያሰበ እንደማይሠራ ነው ያስረዱት፡፡ ሴቶች ከውድድር ይልቅ ትብብርን ፣ ከግለፍተኝነት ይልቅ ሰከን ማለትን የሚያስቀድሙ፣ እንደ ሀገር ያለብንን የግልፍተኝነት፣ የጸበኝነት፣ የእርቅ፣ የሰላም መንፈስ ጉድለት የሚሞሉ ናቸው ብለዋል፡፡
ባልተገባ መንገድ ሕይወታቸውን የሚመሩ ሴቶችን ስንመልስ እነርሱን ብቻ ሳይኾን እንደ ሀገር ያለብንን የስክነት፣ የማሰብ፣ የማስታዋል፣ አርቆ የመመልከት ስብራት ለመጠገን ማዕከሉ በእጅጉ ያግዛል ነው ያሉት፡፡ ሴቶች በኢትዮጵያ ግማሽ ቁጥር ያላቸው ብቻ ሳይኾኑ በሁሉም ሥራዎች ያላቸው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ሴቶችን ማሰብ፣ ማነጽ፣ ማስተማር፣ እድል መስጠት ካልቻልን እንደ ሀገር ለመለወጥ ያለን ሕልምም ሙሉ አይኾንም ነው ያሉት፡፡ በአዲስ አበባ የምናፈርሰው ለማስዋብ እና በኢትዮጵያ ልክ የኾነች ዋና ከተማ ለመፍጠር ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በብዙ ነገር ወደኋላ ቀርታለች መፍጠን ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የማይገኝላት ከተማ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ ሀገር እና ከተማ መሥራቱ በፈተና ውስጥ መኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝቡም ሥራዎችን ለጋራ ጥቅም እንደኾነ በማሰብ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ታላላቅ አጽዋማትን በጋራ እየጾሙ የሚገኙት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ጾሙ ለወደቁ የሚደረስበት ጊዜ በመኾኑ ካላችሁ በማካፈል ደሃ ከኾኑ ወገኖች ጎን እንድትቆሙ አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡
እንተባበር፣ እንተሳሰር፤ ከወሬ ይልቅ ተግባርን እናስቀድም፣ እንስከን፣ እንወያይ፣ እንዋደድ፣ ይቅር እንባባል፣ ሀገራችንን ለመገንባት በኅብረት እንድንቆም አደራ እላለሁ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ያማረች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናስረክባለንም” ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!