
አዲስ አበባ: መጋቢት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሴቶች በፋይናንስ ዘርፉ ተጠቃሚ እንዳይኾኑ የሚያደርጉ ችግሮች ላይ ያተኮረ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ ውይይቱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ በሴቶች ላይ የሚሠሩ ተቋማት እንዲሁም አጋር አካላት በተገኙበት ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በ“ኤፍኤስዲ” ኢትዮጵያ የፋይናንስ አካታችነት ዳይሬክተር አቤል ታደለ ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ የዛሬው መርሐ ግብርም በሴቶች አካታችነት ላይ ከሚሠራው ከ “ፋይን ኢኩይቲ አፍሪካ” ጋር በጋራ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የዓለም ባንክን የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ መሰረት በማድረግ የሴቶችን ዲጂታል የፋይናንስ ተጠቃሚነት በማሳደግ ኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲኾኑ ለማብቃት እየሠሩ እንደኾነም ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶች የፋይናንስ አቅም እያደገ ቢመጣም እንደ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያ እና ኡጋንዳ ያሉ ሀገራት ላይ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ዝቅተኛ ነው ተብሏል።
ሴቶች የፋይናንስ ተጠቃሚ ኾነው ውሳኔ ሰጪ እንዳይኾኑ በፆታ ተጽዕኖ ስር መውደቃቸው እና የተመቻቸ ሁኔታን በገጠርም በከተማም ተደራሽ ማድረግ አለመቻል ተግዳሮት ኾኖ ተነስቷል። የሴቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማሳደግ መሠራት ስላለባቸው ጉዳዮችም የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!