
አዲስ አበባ: መጋቢት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በቀን 2 ሺህ ይታተም የነበረው ፓስፖርት በቀን ከ10 ሺህ በላይ ግላዊ መረጃ እየሰፈረ እየተሠራ እንደኾነ ተናግረዋል።
ባለፈው ስድስት ወራት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ፓስፖርቶች ታትመው ወደ ሀገር ገብተዋል ያሉት ዳይሬክተሯ 640 ሺህ ፓስፖርቶች ደግሞ ግላዊ መረጃ ታትሞባቸው ተሰራጭተዋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ 230 ሺህ፣ በክልሎች 269 ሺህ፣ በአስቸኳይ 35 ሺህ እና 81 ሺህ በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች የፓስፖርት አገልግሎት መስጠት ተችሏል ነው ያሉት፡፡ ዳይሬክተሯ አሁን የቀረው ስርጭት ብቻ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
“80 ሺህ ፓስፖርቶች እጃችን ላይ ይገኛሉ” ብለዋል። መጉላላት እንዳይፈጠር የስልክ መልእክት የደረሳቸው በፍጥነት ፓስፖርት እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
ከመጋቢት 16/2016 ዓ.ም በኋላ ሲስተሙ በሚቀጥረው እና በሚፊቅደው ብቻ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ ስለመኾናቸውም ገልጸዋል። በሁለት ወር ውስጥ ፓስፖርት ማግኘት የሚያስችል አሠራር ስለመፈጠሩም ነው ያስገነዘቡት።
2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ገደማ የሌላ ሀገራት ዜጎች በአየር፣ በየብስ እና በኦን አራይቫል ቪዛ አገልግሎት ስለመሰጠቱም ነው የተናገሩት፡፡የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት በኦን አራይቫል ቪዛ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሚችሉ ሀገራትን ወደ 180 ማሳደግ ስለመቻሉም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!