
ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የእዝነት እና የምህረት ወቅት የኾነውን የረመዷን ወር መልካም ተግባራትን በማከናወን መጠቀም እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኢፍጣር መርሐ-ግብር አካሂዷል።በመርሐ ግብሩ ላይ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር)፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና የኢትዮጵያ ሃማኖቶች ጉባኤ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ “የእዝነት፣ የምህረት እና የመረዳዳት ወቅት የኾነውን የረመዷን ወር መልካም ተግባራትን በማከናወን ልንጠቀምበት ይገባል” ብለዋል።የጠቅላይ ምክር ቤቱ የኢፍጣር መርሐ ግብርም ይህንን ታሳቢ ያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ ሁሌም የሚተገብራቸው መልካም ተግባራት መኖራቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ በረመዷን ወር መልካም ሥራዎች የተለየ ዋጋ የሚሰጣቸው በመኾኑ መትጋት ይገባል ብለዋል።
የረመዷን ወር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተጣላን በማስታረቅ እና ሌሎች መልካም ተግባራትን በማብዛት ሕዝበ ሙስሊሙ እንዲያሳልፍም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የጠቅላይ ምክር ቤቱ የፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ “የረመዷን ወር የተበላሸን በማስታካከል፣ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የምንማርበት የተቀደሰ ወቅት ነው” ብለዋል።ይህንን ታላቅ ዋጋ የሚገኝበትን ወር በመረዳዳት፣ በመተጋገዝ እና ሌሎች መልካም ተግባራትን በማብዛት ማሳለፍ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!