
ባሕር ዳር: መጋቢት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያን እድገት የሚፈሩ ጥቂት ሀገራት የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የባሕር በር ስምምነት እውን ከኾነ ኢትዮጵያ በአካባቢው ኃያልነቷን ታጠናክራለች ከሚል ስጋት ስምምነቱ እውን እንዳይሆን ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡
የኢትዮ-ሶማሌላንድ የባሕር በር ስምምነትን ውስን ሀገሮች ለምን እንደሚቃወሙ፣ ተቃውሟቸው ከምን የመነጨ እንደኾነ እና ኢትዮጵያ በቀጣይ ምን መሥራት እንዳለባት የዘርፉ ምሁራን ምክንያቱን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና የመልካም አሥተዳደር መምህር ተስፋዬ ጂማ (ዶ.ር)፤ የባሕር በር ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ተደማጭ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመኾን ወሳኝ መኾኑንና ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባሕር በር ተጠቃሚ የሚያደርጋትን ስምምነት ከሶማሌላንድ ጋር መፈራረሟን አስታውሰው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲያቆረቁዝና በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን ተደማጭነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለማሳጣት አንዳንድ ሀገራት እንደሚቃወሟት ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር ተጠቃሚ እንዳትኾን የአንዳንድ ሀገራት ተቃውሞ ዋና ምክንያት በአካባቢው የበላይ ኾኖ ለመታየት እና የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር መኾኑን ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ልጠቀም ብላ መጠየቋ እንደወንጀል መታየት የለበትም የሚሉት ዶክተር ተስፋዬ፤ ኢትዮጵያ ለባሕር በር ካላት ቅርበትና የሕዝብ ብዛት አንጻር የማግኘትና የመጠቀም መብት አላት ይላሉ፡፡
ሶማሌ ላንድ ከተለያዩ ሀገሮች ጋር የተለያዩ ስምምነቶችን መፈራረሟን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት እንደ ስህተት ተደርጎ ተወስዶ ሊራገብ አይገባም ይላሉ፡፡
ከሚቃወሙት ሀገራት ግብፅን ለአብነት ያነሱት ዶክተር ተስፋዬ፤ ግብፅ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ካላት ኩርፊያ የተነሳና ኢትዮጵያ በቀይ ባሕርና በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ከተገኘች በአካባቢው የሚኖራትን ተፅዕኖ ያሳጣኛል በሚል ስጋት መኾኑን ያስረዳሉ፡፡
ግብፅ የተለያዩ ደጋፊ ሀገራትን በማሰባሰብ ኢትዮጵያን ወዳጅ ሀገር እንዳይኖራት የማድረግ፣ ሀገሪቱ አለመረጋጋት ውስጥ ገብታ የዓባይ ግድብ ሥራ ላይ እንዳይውል፣ የተለያዩ ስምምነቶችንና ድጋፍ እንዳታገኝ ለማድረግ አስባ እንደምትቃወም ያብራራሉ፡፡
ሀገራት በአካባቢያቸው የሚገኙ የባሕር በሮችን በጋራ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮቻቸውን በማጠናከር የቀጣናቸውን ሠላም ማረጋገጥና ዘላቂ ማድረግ ይችላሉ ይላሉ።
አንድ የባሕር በር አልባ ሀገር የባሕር በር ተጠቃሚ ለመኾን “ሰጥቶ የመቀበል መርሕ”ን መተግበር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የባሕር በር ያላቸው ሀገራትም የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ይገልጻሉ፡፡
አንዳንድ ኃያላን ሀገራት ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ተጉዘው ባሕር በር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚረባረቡት የባሕር በር ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን በመረዳት እንደሆነ ገልጸው፤ ኢትዮጵያም የባሕር በር ለመጠቀም የምታደርገው ጥረት አጠናክራ መቀጠል አለባት ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ሥራዋ ጠንከር በማለት ስምምነቱን በአሉታዊ መልኩ ለተረዱ አካላት የማንንም ጥቅም የማይነካ እና የጋራ ተጠቃሚነትን መርሕ ያደረገ መኾኑን ማሳወቅ ከምሁራንና ከዲፕሎማቶች ይጠበቃል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘትና የመጠቀም ፍላጎቷን እስከምታሳካ ድረስ አጀንዳ ኾኖ ሊቀጥል እንደሚገባ እና ከሶማሌላንድ ጋር የተጀመረውን ስምምነት በቀጣይ ከሱዳን እና ኤርትራም ጋር ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡
የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሙሉጌታ ደበበ (ዶ.ር) በበኩላቸው፤ ሶማሌላንድ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የተለያዩ ስምምነቶችን አድርጋለች፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ስታደርግ አንዳንድ ሀገራት የሚቃወሙት ኢትዮጵያን ወደኋላ በማስቀረት የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር በማሰብ ነው ይላሉ፡፡
ከሚቃወሙት ሀገራት መካከል አንዷ ግብፅ መኾኗን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝ ከሆነ ተደማጭነቷና ኢኮኖሚያዊ እድገቷ ይጨምራል በሚል መኾኑን ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሥነ ምድራዊ አቀማመጥ የብዙ ሀገራት ፍላጎት ያለበት ነው የሚሉት ዶክተር ሙሉጌታ፤ ግብፅም በዓባይ ወንዝ ምክንያት ኢትዮጵያን ከዓለም የኢኮኖሚ መድረክ ለማውጣት የምትጥር ሀገር ብትኾንም የትኛውንም ዓይነት ሴራ ቢሠሩ አይሳካላቸውም ይላሉ፡፡
የባሕር በር የሕልውና ጉዳይ በመኾኑ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ለከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ብቻ የሚተው ጉዳይ ሳይሆን ሁሉም ድጋፍ ሊያደረጉ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ሀገር አቋራጭ ወንዞች ባለቤት በመሆኗ በርካታ ሀገራትን እየመገበች ሲሆን፤ እሷም በሰጥቶ መቀበል መርሕ የትኛውንም ጥቅም የማግኘት መብት እንዳላት ይናገራሉ፡፡
ሀገራት በቀጣናቸው የሚገኝን ባሕር በር በጋራ ሲጠቀሙ አብሮነት፣ ሠላምና በጋራ የመልማት ዕድሎች ይሰፋሉ፡፡ ይህም ሀገራቱ በጋራ እንዲቆሙ በማድረግ በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነታቸው እንዲጨምር ያደርጋል ሲሉ ይገልጻሉ ።
በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባሕር በር ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነትን መርሕ ያደረገ መሆኑን ባለመረዳት አንዳንድ ሀገራት እየተቃወሙ ይገኛል፡፡ ተቃውሟቸውም ጥቅማችን ይነካብናል በሚልና በአካባቢው የበላይ ኾኖ ለመታየት ከመፈለግ የመነጨ መኾኑን ያስረዳሉ፡፡
ጥቅማቸውን ሳይነካባቸውና ጉዳዩ ሳይመለከታቸው ኢትዮጵያን እስከማውገዝ የደረሱ አንዳንድ ሀገራት የሚሰጡት ነቀፋ ተቀባይነት እንደማይኖረው ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ የምታደርጋቸው ማንኛውም ዓይነት ስምምነቶች የጋራ ተጠቃሚነትን መርሕ ያደረጉ መኾናቸውን በሁለትዮሽና በሌሎች የዲፕሎማሲ አማራጮች የማስረዳት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ለቀጣናው በማሰብ ሳይኾን ለራሳቸው ተጠቃሚነት ከመጨነቅ ስምምነቱን እያወገዙ የሚገኙ አካላትን ኢትዮጵያ በሰከነ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እያስረዳች ነው ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርሕ የምታምን ሀገር ናት ያሉት አምባሳደር ፍጹም፤ ለቀጣናው ትስስር እያበረከተች ካለው አስተዋፅዖ በተጨማሪም ለጎረቤት ሀገራት ጋር ጠንካራ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ትስስር መፍጠሯንም ይናገራሉ፡፡
ኢፕድ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው የወደብ ስምምነት ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ለማደግ፣ በመሠረተ ልማትና በንግድ የበለጠ ለመተሳሰር ለምታደርግው ጥረት አንዱ ማሳያ መኾኑንም አምባሳደር ፍጹም ገልጸዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!