የጎጃም ኮማንድፖስት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በአግባቡ በመወጣት የአማራን ክልል ሰላም ማሻሻሉን ሜጀር ጀኔራል ግዛው ኡማ አስታወቁ።

40

ባሕር ዳር: መጋቢት 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮማንድፖስቱ ምክትል ሰብሳቢ እና የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ኦፕሬሽናል ሜጀር ጀኔራል ግዛው ኡማ እንደተናገሩት ኮማንድፖስቱ ሦስት እዞችን በማጣመር ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተሰማራባቸው የጎጃም ዞኖች ሕግ የማስከበር ግዳጁን በስኬት እየፈጸመ ነው ብለዋል።

በዚህም የክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳርን ጨምሮ ሁሉም የዞን፣ የወረዳ እና የቀበሌ ከተሞች እና የገጠር አካባቢዎች በሠራዊታችን ቁጥጥር ስር ገብተዋል። ሕይወቱን ለማትረፍ በየጫካው የተሰገሰገውንም ጽንፈኛ የማደን ተልዕኮው ቀጥሏል ብለዋል።

በተከናወነው ተከታታይ ኦፕሬሽን በመጣው ሰላም መንግሥታዊ መዋቅሩ እንደገና ተጠናክሮ ወደ ሥራ ገብቷል። ተቋርጠው የነበሩ የግብርና፣ የትራንስፖርት፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የባንክ እና ሌሎች አገልግሎቶች እንደገና ሥራ ጀምረዋል። ሕዝቡም የተረጋጋ ኑሮውን በመምራት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

የጎጃም ኮማንድፖስት ከአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ በመኾን ያካሄዳቸው ተከታታይ ስምሪቶች የጽንፈኛውን አከርካሪ ሰብሮ አሽመድምዶታል ያሉት ሜጀር ጀኔራል ግዛው በየጎጡ ተወሽቀው የዘራፊውን ቡድን ሲያስተባብሩ የነበሩትን ጨምሮ በርካታ ኃይሉን ከጥቅም ውጭ አድርጓል። ይጠቀምባቸው የነበሩ የጦር መሳሪያዎች፣ ትጥቆች፣ ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

የጎጃም ኮማንድፖስት የአማራ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥ ባደረጋቸው ውስብስብ፣ እልህ አስጨራሽ እና ጀግንነት የተሞላባቸው ግዳጆች ሕዝቡ የሚፈልገውን ሰላም ማስገኘት ችለዋል። ከተሜው የዕለት ሥራውን፣ አርሶ አደሩም ግብርናውን ያለስጋት እንዲያከናውን አድርገዋል።

ሜጀር ጀኔራል ግዛው ኡማ እንዳሉት ይህ ውጤት የተገኘው የጎጃም ሕዝብ ከሠራዊታችን እና ከአማራ ክልል የጸጥታ ኃይል ጋር አብሮ በመሥራቱ እና የሰላሙ ጠባቂ ራሱ መኾኑን አምኖ ድጋፍ በማድረጉ ነው። የጎጃም ኮማንድፖስትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተሰጡትን ተልዕኮዎች ለማሳካት እንደ እስካሁኑ ሁሉ የሕዝብን ሰላም እና ልማት የሚያሰቀጥሉ ግዳጆቹን በብቃት መወጣቱን ይቀጥላል ብለዋል።

የጀመርነውን ጽንፈኛውን በማሳደድ፣ የገባበት በመግባት፣ በመክበብ እና በመደምሰስ መንግሥት እና ሕዝብ የሰጡንን ተልዕኮ እናሳካለን ሲሉ ተናግረዋል። መረጃው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በተመድ ጥላ ስር የሚሰማራ የሰላም አስከባሪ አስመረቀ።
Next articleከኢትዮ- ሶማሌላንድ የባሕር በር ስምምነት ተቃውሞ በስተጀርባ ያለው ሴራ ምንድን ነው?