የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ ለመመለስ የሕግ እና ፍትሕ ማሻሻያዎችን ለመተግበር እየሠሩ መኾኑን የፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች አሳወቁ።

31

ባሕርዳር: መጋቢት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕግ እና ፍትሕ ማሻሻያዎችን በመተግበር የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየሠሩ እንደኾነ የክልሎች የፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎች ገለጹ።

የፌዴራል ፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት በበኩሉ፤ ክልሎች የሕግ እና ፍትሕ ማሻሻያዎችን በአግባቡ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ድጋፍ እያደረገኩ ነው ብሏል።የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሥራ ኃላፊዎችም የዜጎችን የፍትሕ እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልፀዋል።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ጎሽም በመንግሥት የተደረጉትን የሕግ እና ፍትሕ ማሻሻያዎች ተግባራዊ በማድረግ ለዜጎች ምላሽ በመስጠት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጉዮ ዋሪዮ በሕግ የተደገፈ ባሕላዊ ማኅበራዊ ፍርድ ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ በመግባቱ ለፍትሕ ሥርዓቱ እገዛ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል። የባሕላዊ ፍርድ ቤቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሞዴል ረቀቅ ሕግ ተሞክሮነት የተወሰደ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

በቀበሌ እና ወረዳ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ ደረጃ እና በይግባኝ ሰሚ ተግባራዊ የኾኑት ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችም የፍትሕ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል እገዛ እያደረጉ ነው ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ ገለቱ፤ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ የፍትሕ ዘርፉ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ገልፀዋል። በአዲስ መልክ የተደራጀ ክልል በመኾኑ በፌደራል ደረጃ የተሻሻሉ እና አዲስ የወጡ ሕግጋትን ተግባራዊ ለማድረግ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም ተናግረዋል።

የፌዴራል ፍትሕ እና ሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በለውጡ ዓመታት አሳሪ ሕጎችን በማሻሻል የፍትሕ ዘርፉን በብዙ መልኩ ማስተካከል መቻሉን ተናግረዋል።

በዚህም የዜጎችን የፍትሕ እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አስችሏል ነው ያሉት። የተሻሻሉ እና በአዲስ መልክ ተግባራዊ የተደረጉ ሕጎችን ኢንስቲትዩቱ በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የፍትሕ ዘርፉን እያገዘ ይገኛል ብለዋል። በተለይም በክልሎች የሕግና ፍትሕ ማሻሻያዎች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ ድጋፍና እገዛ እየተደረገ ነውም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምርት ዘመኑ ከ9 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት እየተሠራ መኾኑን የሰሜን ሽዋ ዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
Next articleሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በተመድ ጥላ ስር የሚሰማራ የሰላም አስከባሪ አስመረቀ።