
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያውያን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል። የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ጀውሃር ሙሐመድ የረመዷን ወር የመደጋገፍ እና የመረዳዳት ወር በመኾኑ በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል ድጋፍ ለማሠባሠብ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል። እነዚህን ወገኖች ለማገዝ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በገንዘብም ይሁን በአይነት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሙሐመድ አንዋር በረመዷን ወር የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማገዝ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በረመዷን ወር ይበልጥ ለጋስ እንደነበሩ ያነሱት ሼህ ሙሐመድ ይህንን የነብዩን ቸርነት እና ለጋስነት በታላቁ የረመዷን ወር አማኞች ከተፈናቀሉ ወገኖች ጋር ማሳለፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ሼህ አብዱረህማን ሱልጣን በእስልምና እምነት ረመዷን ወር የመስጠት እና የምጽዋት ወር መኾኑን ገልጸዋል። መረዳዳት ከሃይማኖታዊ እሴትነቱ ባለፈ ግብረ ገባዊ እሴትነቱ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የጠነከረ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ የመስጠት እና የመረዳዳት ወር በኾነው የረመዷን ወር “ጾማችን ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን” በሚል ሀሳብ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሠብሠብ ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ነው የገለጹት። ከመጋቢት 6/2016 ዓ.ም ጀምሮ የማሠባሠብ ሥራው በይፋ ይጀመራል ተብሏል። በሁሉም ዞኖች የሚገኙ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤቶች እንዲያስተባብሩም ጥሪ ቀርቧል።
69 ሺህ 630 የሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ መታቀዱ ነው የተገለጸው።
እነዚህን ወገኖች ለማገዝ የሚፈልግ መንግሥታዊ ኾነ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት እንዲሁም በሀገር ውስጥም ኾነ ከሀገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማንኛውንም አይነት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። በገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም አካል ከዚህ በታች በተቀመጡት የባንክ አካውንቶች ድጋፍ ማድረግ ይችላልም ተብሏል።
1. ዳሽን ባንክ = 7902070047911
2.ሂጅራ ባንክ = 1005297390001
3. ፀሐይ ባንክ = 1004462781
4. አቢሲኒያ ባንክ = 178744844
5. ንግድ ባንክ = 1000621977777
በቀጣይ የአማራ ባንክ እና ዘምዘም ባንክ የአካውንት ቁጥር እንደደረሰ ምክር ቤቱ ለማኅበረሰቡ ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል። አጠቃላይ ሂደቱንም ምክር ቤቱ በየጊዜው ለማኅበረሰቡ ይፋ እንደሚያደርግ ተነስቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!